የውሃ አካላት ደህንነትን ለማስጠበቅ የስነ አካላዊ የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ስራዎችን የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ።

የውሃ አካላት ደህንነትን ለማስጠበቅ የስነ አካላዊ የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ስራዎችን የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ። አሶሳ: የካቲት 08/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የስነ-አካላዊ ስራዎችን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ኡራ ወረዳ አምባ ሁለት ቀበሌ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር አካሄደ። መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ "አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት" በሚል መርህ ለተከታታይ አመታት ከህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅ/ቤትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበረ አንስተው፤ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ከባቢያዊ ጠቀሜታን አስተማማኝ ለማድረግ እና ህልውናውን ለመጠበቅ የተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በሀገራችን ልዩ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማትና እንክብካቤ ስራው ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ አልሄደም ያሉት ክቡር አቶ ሞቱማ ተፋሰስ ድንበር ስለሌለው የውሃ ፍሰቱን ተከትሎ የሚሄድ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከተው አካል ተባብሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። የተቀናጀ የውሃ ሀብት ልማት፤ እንክብካቤ እና አጠቃቀምን በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ለማስፈን በተፋሰሱ ውስጥ ካሉ ባለድርሻ አካላትና ተቋማት ጋር በመቀናጀት እና በመተባበር የስነ-አካላዊ ስራዎችን በሚከናወኑበት አግባብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ምክክር መድረክ ላይ በሰፊው ውይይት ይደረጋል ብለዋል። በመርሀ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበከር ኸሊፋ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻዎች ሁለት ወር የሚቆይ ስራ ሲሆን በጥራት በመስራት የአካባቢው ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል። የክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ደሳለኝ በበኩላቸው ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ለመስራት ታቅዶ የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፤ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ የስነ አካላዊ ስራዎችን ለመስራት እንደሀገር ጥር 06 እንደ ክልል ደግሞ ጥር 15/2017 ዓ.ም ይፋ መደረጉን አንስተዋል። አቶ ፈቃዱ አክለውም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የአባይ ተፋሰስ ፅ/ቤት፣ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተው አብዛኛው ስራና ወጪ የአካባቢው ማህበረሰብ የሚሸፈን መሆኑን ገልፀዋል።

Share this Post