በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል፣ ለሲዳማ ክልልና ለዞን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል፣ ለሲዳማ ክልልና ለዞን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ። ግንቦት 18/2015ዓ.ም (ው. ኢ. ሚ) ከውሃ ሀብት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የህግ ማእቀፎች፣ ስለተፋሰስ እቅድ ምንነትና የውሃ ሀብት አጠቃቀም ተግዳሮቶችና መረጃዎች እንዲሁም የውሃ አካላት ደህንነት ዙሪያ ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል፣ ለሲዳማ ክልልና ለዞን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ። መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሀይድሮሎጂና የተፋሰስ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ እንደገለፁት እንደ ሀገር ምንም እንኳን በቂ የዝናብ መጠን፣ በርካታ ወንዞች፣ ሀይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት ያሏት ቢሆንም የዝናብ መጠኑ በቦታና በጊዜ ያለው ስርጭት የተዛባ በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብት መራቆት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት የተነሳ ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ገልፀው በውሃ አካላት ዙሪያ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ውሃን ማእከል አድርገው ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እቅድ እንዲኖርና ሁሉም የውሃ ተጠቃሚ በፍቃድ ላይ የተመሰረተ አጠቃቀምን በመገንዘብና በመተግበር ከውሃ ሀብታችን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን፤ የውሃ ብክለትንና ብክነትን መከላከል እንደሚገባ ገልፀዋል። አቶ ደበበ አያይዘውም ክልሎቹ በከፍተኛ የዝናብ መጠን፣ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት፣ የኢንዱስትሪና የከተሞች መስፋፋት ያለባቸው እንደመሆኑ ያሉትን እድሎች በመጠቀም ማህበረሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ በመሆን ተጨባጭ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ገልፀዋል። የስልጠናው መርሀ ግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፋት የደቡብ ክልል የውሃ፣ መስኖና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው በክልሉ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በጋራ እንዲሰሩ አሳስበዋል። ስልጠናው በክልልና በዞን ደረጃ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመምራትና ለማልማት እየሰሩ ባሉት አካላት መካከል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው።

Share this Post