ብሔራዊ ጥቅምና ጂኦ-ስትራቴጂ ቁመና በሚል አጀንዳ ውይይት ተደረገ።
ጥቅምት 07/2018 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ብሔራዊ ጥቅምና ጂኦ-ኢስትራቴጂ ቁመና በሚል ሀገራዊ አጀንዳ ላይ በጋራ ተወያይተዋል ።
ለውይይት መድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ለአንድ ዜጋ ህልውና ሀገር ወሳኝ መሆኑን ሀገራቸው የፈረሰባቸውን ሶሪያን፣የመንን፣ሊብያንና ሶማሊያን ለአብነት አንስተው እንደ ዜጋ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለብሔራዊ ጥቅምና ለሀገራዊ አንድነት የበኩሉን ማበርከት አለበት ብለዋል።
ሀገር ማለት ህዝብ ፣ድንበር ፣ሉዐላዊነትና መንግስት ነው የሉት ክቡር ሚኒስትሩ ከነዚህ አንዱ ከተጓደለና ብሔራዊ ጥቅሟ ካልተጠበቀ ሀገር አትቀጥልም ብለዋል።
ሀገራዊ ህልውናና ደህንነት ፣ኢኮኖሚ ብልፅግና፣ፖለቲካ አቅምና ተጽኖ ፈጣሪነት፣የባህል ነፃነትና ተጽኖ ፈጣሪነት እና የህዝቦች ማህበራዊ ልማት
የብሔራዊ ጥቅሞች ቁልፍ ግቦች እንደሆኑም አብራርተዋል።
የብሔራዊ ጥቅማችን ዋነኛ ፈተናዎች የታሪካዊ የጠላቶቻችን ያልተገራ ዘመን ተሻጋሪ ፍላጎትና ተያያዥ ጉዳዮች መሆናቸውንም ክቡር ሚኒስትሩ በመነሻ በጽሑፋቸው አንስተዋል።
በመጨረሻም እንደ ሀገር በታደሰ ቁመና አዲሱን ዓለም መዋጀት፣ የጠላትን የውጊያ አቅም መስበር እንዴት እንደሚቻል፣የመንግስት ተቋማት ሚና ምን እንደሆነና እያንዳንዱ ዜጋ ምን መወጣት አለበት የሚሉ ጉዳዮችን በዝርዝር አንስተዋል።
በመነሻ ጽሑፉ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።