የብሔራዊ አንድ ቋት ፕሮግራም (One WASH national program ) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የብሔራዊ አንድ ቋት ፕሮግራም (One WASH national program ) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የብሔራዊ አንድ ቋት (One WASH National Program) ፕሮግራም የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ አያካሄደ ነው።
በግምገማው በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎች፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች በስፋት ተዳሰዋል።
ፕሮግራሙ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የንጽህና እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን በተቀናጀና በዘላቂ መንገድ ለማዳረስ መሆኑ ተጠቅሷል።
በመነሻ እቅዱም 3.8 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ እስካሁን በተለያዩ ፕሮጀክቶች በተከናወኑ ሥራዎች 3.28 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ ፕሮግራሙ ጥሩ አፈጻጸም እንዳሳየ ተገልጿል።
በግምገማው ላይ የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የፕሮግራሙ የክትትልና ግምገማ እስፔሻሊስት አቶ ታሪኩ አብዲሳ፣ የፕሮግራሙን አጀማመር፣ የትግበራ ሂደት፣ የተፈጸሙ የፋይናንስና የፊዚካል ሥራዎች፣ የበጀት አጠቃቀም፣ በሂደት የታዩ ለውጦች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በተጨማሪም በገጠርና በከተማ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማስፋፋት፣ የንጽህናና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ድርቅን ለመቋቋም የተከናወኑ ሥራዎች ለውይይት ቀርበዋል።
በፕሮግራሙ ስር ከሚኒስቴሩ ጋር ውል ገብተው በተለያዩ አካባቢዎች ፕሮጀክቶችን የሚያስፈጽሙ አማካሪዎች የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን እያቀረቡ ነው።
በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር
ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፣የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች፣መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች እየተሳተፉበት ነው።
ከግምገማው የሚሰበሰቡ ግብዓቶች በቀጣዩ በጀት ዓመት ፕሮግራሙን የበለጠ ውጤታማና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።