በHCO ፕሮጀክት በኢነርጂው ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዠ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በHCO ፕሮጀክት በኢነርጂው ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዠ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ሰኔ 3/2018 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በHuman Capital Operation (HCO) ፕሮጀክት ማዕቀፍ ለፌዴራል፣ ለክልል እና በወረዳ ደረጃ ላሉ ባለሙያዎች በኢነርጂው ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዠ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ።

የስልጠና መርሃ ግብሩ የ2018 በጀት ዓመት የሰው ኃይል ልማት እቅድ አካል ሲሆን፣ በኢነርጂ ዘርፍ የቴክኒክ እውቀትና ክህሎት በማሳደግ የታዳሽ ኃይል ልማት ሥራዎችን የበለጠ ውጤታማና ዘላቂ ለማድረግ ያለመ ነው።

የስልጠናውን መክፈቻ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ሲሆኑ፣ HCO ፕሮጀክት በኢትዮጵያ እና በዓለም ባንክ ትብብር የሚተገበር የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ገለጻ፣ ፕሮግራሙ የመሠረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ጥራት፣ ተደራሽነት እና ቀጣይነት በማሻሻል በውሃ፣ በሳኒቴሽን፣ በጤና፣ በትምህርት እና በኢነርጂ ዘርፎች የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና አለው።

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ በንጹህ ኃይል ልማት ዘርፍ አስደናቂ እመርታ እያሳየች መሆኗን ጠቅሰው፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ከታዳሽ ምንጮች እንደሚመነጭ ተናግረዋል።

የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አውታረ መረብም በአብዛኛው በውሃ ኃይል ላይ የተመሰረተ አረንጓዴ ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት፣ እውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም የተቋማትን አቅም ለማሳደግ በቀጣይነት እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በውሃ፣ በንፋስ፣ በፀሐይ፣ በባዮጋዝ እና በጂኦተርማል ኃይል ከፍተኛ እምቅ አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ፣ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ልማትና ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠናው በንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂዎች (Clean Cooking Solutions)፣ በንጹህ ማብሰያ ቴክኒካል ፓራሜትሮችና ዝርዝር መስፈርቶች፣ በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ልማት አጠቃላይ እይታ፣ በSolar Energy Design and Specifications፣ በባዮጋዝ ልማት እና በBiogas Technology Installation ቴክኒካል መስፈርቶች ዙሪያ ጥልቅ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ነው ክቡር አምባሳደሩ የገለጹት ።

ስልጠናው በኢነርጂ ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት፣ ውጤታማ አስተዳደር እና ዘላቂ የልማት ውጤቶችን ለማምጣት ጠንካራ መሠረት እንደሚሆንም አክለው ገልጸዋል።

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው በመጨረሻ ይህ ስልጠና የእውቀት ማካፈያ ብቻ ሳይሆን የልምድ ልውውጥ፣ የችግር መፍቻ እና የጋራ አቅም ማጎልበቻ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተሳታፊዎች በሙሉ ትኩረት በመሳተፍ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ደጉማ የጤና ሚኒስቴር እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት በበርካታ የልማት ፕሮግራሞች ላይ በጋራ በመስራታቸው ውጤታማ ለውጦችን ማምጣት መቻላቸውን አስታውሰው ፤ አመራሮች በቅንጅት ሲሰሩ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል በተግባር መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

“ውሃና ጤና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ያሉት ክቡር ዶ/ር ደረጀ፣ ጤና የበርካታ ዘርፎች ውጤት በመሆኑ ውሃና ኢነርጂ ከሌለ ጤናማ ማህበረሰብ መገንባት እንደማይቻል ገልጸዋል።

በተመሳሳይም በትምህርትና በግብርና ዘርፎች መሠረታዊ ለውጥ ካልተፈጠረ የጤና ውጤቶችን ማሻሻል አዳጋች መሆኑንም አመልክተዋል።

ክቡር ዶ/ር ደረጀ በዚሁ አጋጣሚ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የጤናውን ዘርፍ እንደራሳቸው በመመልከት ለተደረጉ የጋራ ሥራዎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይም በብሔራዊ ዋን ዋሽ (One WASH National Program) ፕሮግራም ክቡር አምባሳደሩ በመሩት ስቲሪንግ ኮሚቴ እና በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ንጹህና በቂ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ በተጨባጭ ውጤት የታጀበ የጋራ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢኒሼቲቭ የሆነው “ጽዱ ኢትዮጵያ” ፕሮግራም አካል በሆነው ሥራ፣ የጤና ተቋማት ንጹህ፣ ምቹ እና ለታካሚዎች ተስማሚ እንዲሆኑ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት እንዲጠናከር ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላው የሁለቱ ተቋማት የጋራ ትኩረት የሆነው Human Capital Operation (HCO) ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ክቡር ዶ/ር ደረጀ፣ ፕሮጀክቱ በውሃ፣ በጤና፣ በግብርና እና በማህበራዊ ዘርፎች የተቀናጀ ልማት በማምጣት ጤናማና የተማረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የአሁኑ ስልጠናም የፕሮጀክቱ አካል በሆነው የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በተለይ ንጹህ የማብሰያ ኢነርጂዎችን በቤተሰብ ደረጃ ለማስፋፋት እና የቤት ውስጥ የጭስ ብክለትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተባባሰ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም አማራጭ ንጹህ የማብሰያ ኢነርጂዎችን ማስፋፋት እና ማህበረሰቡን በዚህ ዙሪያ ማብቃት ወሳኝ በመሆኑ፣ በዚህ ዘርፍ የሚሰጡ ስልጠናዎች ለሀገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

ስልጠናው ለቀጣይ ሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ከፌደራል ፣ ከክልል ፣ከዞንና ወረዳ የተውጣጡ የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎችና ሙያተኞች እየተሳተፉ ነው።

Share this Post