ኢትዮጵያ በEAPP ስብሰባ የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ገበያ (Day-Ahead Market) በአስቸኳይ እንዲጀመር ጥሪ አቀረበች፡፡
ኢትዮጵያ በEAPP ስብሰባ የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ገበያ (Day-Ahead Market) በአስቸኳይ እንዲጀመር ጥሪ አቀረበች፡፡
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በ37ኛው ልዩ የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር (EAPP) የስቲሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ገበያ (Day-Ahead Market-DAM) በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገባ ጥሪ አቀረበች።
መንግሥት የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ገበያው መዘግየት አባል ሀገራት ከድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ንግድ የሚገኙ ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ጥቅሞችን እንዳይጠቀሙ እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ተጨማሪ መዘግየት የቀጠናውን የኃይል ትስስር ግቦች እንደሚያስተጓጉል በመግለጽ፣ ገበያው በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል።
ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው 37ኛው ልዩ የEAPP የስቲሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ኢትዮጵያ ለቀጠናዊ የኃይል ትስስር ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠው፣ በአስተዳደር ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይቶች እየቀጠሉ ቢሆንም የDAM ሥራ እንዲጀምር ተግባራዊ ውሳኔ እንዲወሰድ አባል ሀገራትን አሳስበዋል።
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የውሃ፣ የጂኦተርማል፣ የንፋስና የፀሐይ ኃይል ሀብቶች ቢኖሯትም፣ በክልሉ ያሉ ሚሊዮን ዜጎች አሁንም አስተማማኝና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኙ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የክልላዊ የኃይል ትስስር መጠናከር የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የኃይል ደህንነትን ለማጠናከር፣ የኤሌክትሪክ ዋጋን ለመቀነስና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ከሚያስችሉ ውጤታማ መንገዶች አንዱ መሆኑን አስምረዋል።
ኢትዮጵያ በተጨማሪም EAPP በቅርብ ዓመታት በክልሉ የኃይል ትስስርን ለማጠናከር ያስመዘገበውን ጉልህ እድገት አድንቃለች። ከእነዚህም መካከል የኢንተርኮኔክሽን ኮድ ተገዢነት ፕሮግራም ተግባራዊ መሆኑ፣ የክልሉ የአሠራር ዝግጁነት መሻሻሉ፣ የDay-Ahead Market የንግድ መድረክ በተሳካ ሁኔታ መግጠሙና መፈተሹ፣ እንዲሁም የEAPP ገለልተኛ የቁጥጥር ቦርድ (IRB) ሴክሬታሪያት በዩጋንዳ መቋቋሙ ተጠቃሽ ስኬቶች መሆናቸውን ገልጻለች።
ሆኖም ለDAM ሥራ መጀመር የሚያስፈልጉ ቴክኒካል ዝግጅቶች ከአንድ ዓመት በፊት ቢጠናቀቁም፣ ገበያው እስካሁን ወደ ንግድ ሥራ አለመግባቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጻለች። የዚህ ዋና መሰናክልም በEAPP የአስተዳደር ማዕቀፍ ላይ በቀረቡ የማሻሻያ ሀሳቦች ዙሪያ አባል ሀገራት የጋራ ስምምነት አለመድረሳቸው መሆኑን ጠቁማለች።
በዚህ ምክንያት አባል ሀገራት ከተስፋፋ የክልላዊ የኤሌክትሪክ ንግድ የሚገኙ ጥቅሞችን እንዳላገኙ በማመልከት፣ በኢንተር-ገቨርንመንታል ሜሞራንደም ኦፍ አንደርስታንዲንግ (IGMOU) እና በኢንተር-ዩቲሊቲ ሜሞራንደም ኦፍ አንደርስታንዲንግ (IUMOU) ላይ የሚደረጉ የማሻሻያ ውይይቶች እየቀጠሉ ባሉበት ሁኔታ፣ የDAM ገበያው በአሁኑ የአስተዳደር አወቃቀር ስር ሥራውን እንዲጀምር የስቲሪንግ ኮሚቴው እንዲያጤን ጥሪ አቅርባለች።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የEAPP የስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEP) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የEAPP ዋና ጸሐፊ ኢንጂነር ጄምስ ዋሆጎ ተሳትፈዋል።
በስብሰባው የሰው ኃብትና አስተዳደር ኮሚቴ እና የሕግ ባለሙያዎች በIGMOU እና IUMOU ላይ ያዘጋጁት የማሻሻያ ረቂቆች የደረሱበትን ደረጃ ገምግመዋል። እነዚህ ምክረ ሀሳቦች በሐምሌ 3 እና 4ቀን 2018 ዓ.ም. ) ለሚካሄደው 22ኛው ልዩ የEAPP የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ለውሳኔ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ በመጨረሻ አባል ሀገራት በክልላዊ የኃይል ትስስር፣ በተቆጣጣሪ ትብብርና በገበያ ዝግጁነት የተገኘውን እመርታ በማስቀጠል፣ የክልላዊ የኤሌክትሪክ ንግድን የሚያፋጥኑ እና የተቀናጀ የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ገበያ እውን እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን በቅድሚያ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።
37ኛው ልዩ የEAPP የስቲሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ በEAPP የወደፊት አስተዳደር ማሻሻያ እና በቀጠናዊው የኤሌክትሪክ ገበያ ሥራ ማስጀመር ዙሪያ ለ22ኛው ልዩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል።