የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የስቲሪንግ ኮሚቴ የ2018 ዓ.ም. አፈጻጸምን በመገምገም የ2019 ዓ.ም. ዕቅድን አጸደቀ።

የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የስቲሪንግ ኮሚቴ የ2018 ዓ.ም. አፈጻጸምን በመገምገም የ2019 ዓ.ም. ዕቅድን አጸደቀ።

ሰኔ 25/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.)

የብሔራዊ ዋን ዋሽ (One WASH National Program–OWNP) የስቲሪንግ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በራዲሰን ብሉ ሆቴል በማካሄድ የ2018 ዓ.ም. አጠቃላይ የፕሮግራሙን አፈጻጸም በመገምገም የ2019 ዓ.ም. ዕቅድን አጽድቋል።

በስብሰባው የ2018 ዓ.ም. በፕሮግራሙ ሥር የተከናወኑ የውሃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽንና የሃይጅን (WASH) ሥራዎች አፈጻጸም በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸው ተገልጿል።

በሪፖርቱ መሠረት የፕሮግራሙ አፈጻጸም ጥሩ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ በቀሪው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ፣ የተቋማት ቅንጅትና ትብብርን የበለጠ ማጠናከር፣ የውሃ ተቋማትን ዘላቂ አሠራር፣ ጥገናና አስተዳደር ማጠናከር እንደሚገባ የኮሚቴው አባላት አሳስበዋል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ (Climate-Resilient) የWASH ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ፣ የፕሮግራሙ ክትትል፣ ግምገማ፣ ሪፖርትና የፋይናንስ ግልጽነት የበለጠ እንዲጠናከር አባላቱ ጠይቀዋል።

በስብሰባው የተነሱ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንገሞ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

ክቡር አምባሳደሩ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላትን፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮችን እንዲሁም የልማት አጋሮችን በ2018 ዓ.ም. ለተመዘገበው አፈጻጸም አመስግነው፣ የተጀመሩ የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በቀሪው ጊዜ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል።

የውሃ ተቋማት ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሥርዓት አስተዳደር ሞዴል ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልጸው፣ በሌላ በኩል የኢነርጂ ጉዳይ በተለይም ከነዳጅ ዋጋ መጨመርና ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር የሶላር ኢነርጂ አጠቃቀም በሞዴሉ ውስጥ መካተቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ክቡር አምባሳደሩ እንዲሁም የውሃ፣ ጤና፣ ትምህርትና ፋይናንስ ተቋማት በ“One Plan, One Budget, One Report” መርህ መሠረት በተቀናጀ አሠራር እየሠሩ መሆኑ የተሻለ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በተለይ በገጠርና አገልግሎት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ማስፋፋት የቀጣይ ትኩረት እንደሚሆን ገልጸው፣ የደህንነት ተግዳሮት ባለባቸው አካባቢዎችም በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ለተመዘገበው ውጤት የክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንገሞን አመራር አመስግነው፣ የፕሮጀክቶች ዘላቂነት በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው የሥራ አቅጣጫ መሠረት በቀሪው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጥሪ አቅርበው፣ ለዚህም የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ በበኩላቸው፣ የፕሮግራሙ አፈጻጸም ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በምዕራፍ ሁለት የገጠር መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች 96 በመቶ የተከናወኑ ሲሆን፣ በትምህርትና በጤና ተቋማት የታቀዱ ፕሮጀክቶች 100 በመቶ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በ7 መካከለኛ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን እና ከ43 አነስተኛ ከተሞች 28ቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ፣ ቀሪዎቹ በተለያየ የግንባታ ደረጃ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በCR-WASH ፕሮጀክትም 6 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ከ70 እስከ 90 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና በቀጣይ ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ኮሚቴው የ2019 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድን በማጽደቅ፣ በቀጣይ ዓመት የፕሮግራሙ ትኩረት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ የሳኒቴሽንና ሃይጅን አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ የፕሮጀክቶች ዘላቂነትን ማረጋገጥ እና በተቀናጀ አሠራር የፕሮግራሙን ውጤታማነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚሆን አቅጣጫ አስቀምጧል።

Share this Post