ውጤታማ የኢነርጂ ልማት ለግብርናና ለኢንዱስትሪ ማንሰራራት

ውጤታማ የኢነርጂ ልማት ለግብርናና ለኢንዱስትሪ ማንሰራራት

ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም. (ዉ.ኢ.ሚ)

የመደመር መንግሥት በኢነርጂ ልማት ባከናወናቸው በርካታ ተግባራት አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። የኢነርጂ አማራጭ ምንጮችን በአግባቡ በመለየት እና በጠንካራ የፕሮጀክት አፈጻጸም በዘርፉ የላቀ ስኬት መጥቷል።

የኢነርጂ አማራጭን በማስፋት ከውሃ በተጨማሪ የንፋስ፣ የፀሐይ እና የእንፋሎት ኢነርጂን በማልማት የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ተሰርቷል።

የኃይል ተደራሽነት መስፋፋቱ የተለያዩ ዘርፎች ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ወሳኝ ሚና አለው። በተለይም የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በማድረግ ለአገራዊ ብልጽግና እውን መሆን የድርሻውን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ሥራዎች አጠቃላይ የኃይል ተደራሽነት 63 በመቶ ደርሷል። ይህም ከግሪድና ከኦፍ-ግሪድ የኃይል አቅርቦቶች የተገኘ ውጤት ሲሆን፤ ከተሞችን እና ገጠር አካባቢዎችን በኃይል አገልግሎት ለማስተሳሰር የተደረገውን ጥረት ያሳያል።

የኢነርጂ ልማት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማሳደግ ባለፈ፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ደማቅ አሻራውን እያሳረፈ ነው። ኃይል ለግብርናና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች የምርት መሠረታዊ ግብዓት በመሆኑ የእነዚህን ዘርፎች ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው።

የኃይል አቅርቦት መስፋፋቱ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፣ የግብርና ማሽነሪዎችን በስፋት ለመጠቀም፣ የውሃ ማንሳትና ማከፋፈል ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እንዲሁም የምርትና የማቀነባበር አቅምን ለማሳደግ እያገዘ ይገኛል። በዚህም የግብርና ምርትን ከማሳ እስከ ገበያ የሚያስተሳስር የምርት ሰንሰለት ለማጠናከር አዳዲስ ዕድሎች ተፈጥረዋል።

በኢንዱስትሪውም የተረጋጋና ተደራሽ የኃይል አቅርቦት የፋብሪካዎችን፣ የማምረቻ ተቋማትንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የምርት አቅም ለማሳደግ ወሳኝ ግብዓት ሆኗል። የኃይል አቅርቦቱ መሻሻል የማምረቻ ሂደቶችን ለማሳለጥ፣ የምርት ወጪን ለመቀነስ፣ የምርት መጠንና ጥራትን ለማሳደግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያግዛል።

የግሪድና ኦፍ-ግሪድ የኃይል መፍትሔዎችን በጋራ መጠቀምም ከብሔራዊ ግሪድ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን በኃይል አገልግሎት ለማካተት የሚያስችል አማራጭ ፈጥሯል። ይህም በገጠር የሚገኙ አነስተኛ ንግዶችንና የማምረቻ ተቋማትን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና የአካባቢ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት ዕድል ፈጥሯል።

የኃይል ተደራሽነት መስፋፋቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂና በዲጂታል አገልግሎቶች የሚታየውን ለውጥ ለማፋጠን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ኃይል ከቤት ብርሃን በላይ የምርት፣ የኢንተርፕራይዝ፣ የኢንዱስትሪና የዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረት በመሆኑ የኢነርጂ ልማት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን የማይተካ ሚና አለው።

በመሆኑም የኢነርጂ ልማትን ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከከተማ ልማትና ከሌሎች ዘርፎች ጋር በማስተሳሰር መሥራት የኢትዮጵያን የምርት አቅም ለማሳደግና የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማፋጠን ቁልፍ ነው።

በአጠቃላይ የኃይል ተደራሽነት የኤሌክትሪክ ብርሃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርታማነት ዕድገት መሰረት ሆኗል።

በተጨማሪም የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ የልማት ደረጃ ለማሸጋገር የኢነርጂ ዘርፉ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ይህንን ድርሻውን ይበልጥ ለማጠናከር እና አገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የኢነርጂ ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

Share this Post