ጤናማ ሠራተኛ፣ ለላቀ የተቋም ውጤታማነት!
ጤናማ ሠራተኛ፣ ለላቀ የተቋም ውጤታማነት!
ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም. – (ውኢሚ)
ስፖርት የአካል ብቃትን ከማሻሻል ባለፈ የሠራተኞችን ጤና፣ አብሮነት፣ ትብብርና የሥራ ውጤታማነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው። ይህንን በመገንዘብ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች ከ2017 ዓ.ም. ህዳር ወር ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው የአካል ብቃት ሥልጠና በመሳተፍ ጤናቸውንና የሥራ ብቃታቸውን እያሻሻሉ ይገኛሉ።
የሚኒስቴሩ ONE LOVE HEALTH SPORTS TEAM በሠራተኞች መካከል የአካል ብቃት ባህልን ለማዳበር፣ ጤናማ አኗኗርን ለማበረታታትና የቡድን መንፈስን ለማጠናከር በትጋት እየሠራ ይገኛል።
ይህንን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሀሳብ በማመንጨት፣ በማበረታታትና በቀጣይነት እንዲተገበር በማድረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ጉልህ ሚና አላቸው። የሠራተኞች ጤና ከሥራ ውጤታማነት፣ ከተቋማዊ አብሮነትና ከጠንካራ የሥራ ባህል ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን በመገንዘብም ለእንቅስቃሴው ቀጣይ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአካል ብቃት ሥልጠናው በሠራተኞችና በቤተሰቦቻቸው ጤና ላይ አዎንታዊ ለውጥ ከማምጣቱም በላይ በሠራተኞች መካከል ተግባቦትን፣ መተባበርንና አብሮነትን እንዳጠናከረ ገልጸዋል።
የስፖርት ቤተሰቡ አሰልጣኝ አዳነ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ክብርና አድናቆቱን በመግለጽ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋም የአካል ብቃት ባህሉ ከሠራተኞች አልፎ ወደ ቤተሰቦች እንዲስፋፋ በማሰብ፣ ተሳታፊዎች የትዳር አጋሮቻቸውንና ሌሎች የቤተሰብ አባላትን ወደ ሥልጠናው እንዲያመጡና እንዲያሳትፉ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም ጤናማ አኗኗርን ከሥራ ቦታ ባሻገር በቤተሰብ ደረጃ ለማስፋፋት ያግዛል።
የስፖርት ቤተሰቡ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የአካል ብቃት ሀሳቡን በማመንጨት፣ በማበረታታትና በተግባር እንዲውል በማድረግ ለሠራተኞች ጤና፣ ለተቋሙ አብሮነትና ለጠንካራ የሥራ ባህል ላበረከቱት አስተዋፅዖ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል።
ለስፖርተኞቹ የሻወር አገልግሎት፣ የልብስና የገላ ሳሙና የመሳሰሉ አገልግሎቶች መቅረባቸውም ለእንቅስቃሴው የሚደረገው ተጨማሪ ተቋማዊ ድጋፍ አካል ናቸው።
በአጠቃላይ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሠራተኞች ጤናማ፣ ተባባሪና ውጤታማ እንዲሆኑ ከማገዝ ባለፈ፣ በሥራ ቦታ የአብሮነት፣ የትብብርና የመረዳዳት ባህልን እያጠናከረ ይገኛል።
ጤናማ ሠራተኛ፣ ጠንካራ ቡድን፣ ውጤታማ ተቋም!