የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የ2018 ዓ.ም. ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ግምገማው በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም የተገኙ ውጤቶችን፣ የታዩ ተግዳሮቶችን እና ለቀጣይ ዘመን የሚወሰዱ የማሻሻያ አቅጣጫዎችን ለመለየት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት (flood management project) ሲቀረጽ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው በሃገሪቱ ጎርፍ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸውን አካባቢዎች የሚደቀንባቸውን የአደጋ ስጋት ለመቀነስና ከችግሩ ለማላቀቅ እንዲቻል በአዋሽ፣በኦሞ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ዙሪያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን መሆኑን የፕሮጀክቱ የቴክኒክ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ አባቡ የፕሮጀክቱን የአፈጻጸም ሪፓርት በመድረኩ ላይ ባቀረቡበት ወቅት አስረድተዋል።

በአለም ባንክ የሚደገፈው ይህ ፕሮጀክት 635,000 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ በበጀት ዓመቱ ስራዎችን ሲተገብር የቆየ ሲሆን እስከአሁን ድረስ 277,389 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉም በመድረኩ ተገልጿል ።

በሪፖርቱ በዓመቱ በጎርፍ ስጋት በሚታዩ አካባቢዎች የተከናወኑ የመከላከልና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በዝርዝር ቀርበዋል።

ከተከናወኑት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የወንዝ ዳርቻ የማስፋፋት ሥራዎች፣ በወንዞች የተከማቸ ደለል የማውጣት ሥራዎች፣ የጎርፍ መከላከያ ግድብ (Dike) ግንባታና ማጠናከሪያ ሥራዎች፣ የጎርፍ ስጋትን የሚቀንሱ የመከላከያ መሠረተ ልማቶች እና ሌሎች የቴክኒክ ጣልቃ ገብነቶች የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህ ሥራዎች በተለይ በዝናብ ወቅት በሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ላይ የሚደርሰውን የሕይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ ያላቸው ሚናም ተብራርቷል።

በተጨማሪም የጎርፍ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከኢንዱስትሪዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ የኢንዱስትሪ–ዩኒቨርሲቲ ቁርኝት ፕሮግራሞች እና ለዘላቂ የጎርፍ አስተዳደር የሚያገለግል የመመሪያ (Guideline) ሰነድ ዝግጅት ላይ የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፓርቱ አብራርቷል።

ከቴክኒካዊ ሥራዎች ባሻገር ለክልሎች፣ ለባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት የተሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓቶች ማጠናከር፣ የግዥና የኮንትራት አስተዳደር ሂደቶችን ማሻሻል እንዲሁም የፕሮጀክት ትግበራን የሚያሳልጡ የአስተዳደር ማሻሻያዎች በዝርዝር ቀርበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ኮንሰልታንቶችም በኃላፊነታቸው ሥር ያከናወኗቸውን የጥናት፣ የዲዛይን፣ የክትትልና የቴክኒክ ድጋፍ ሥራዎች በማቅረብ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ አፈጻጸም የሚያሳዩ ግኝቶችንና ምክረ ሀሳቦቻቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም በክቡር ሚኒስትሩ የመድረክ መሪነት በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፣ በውይይቱ የተገኙ አስተያየቶችና ምክረ ሀሳቦች የቀጣዩን የሥራ ዘመን እቅድ ለማሻሻልና የጎርፍ መከላከል ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ግብዓት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

በግምገማ መድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትርክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ፣ መካከለኛ አመራሮች፣ የሜትሮሎጂ፣ የአደጋ ስጋት አመራሮች ፣ ባለሞያዎች፣ አማካሪዎች፣ ኮንትራክተሮች፣ ኮንሰልታንቶች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተው በፕሮጀክቱ አፈጻጸምና በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ሀሳብ በመለዋወጥ ተሳትፈዋል።

Share this Post