የጎርፍ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ለማጠናከር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተካሄደ።
የጎርፍ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ለማጠናከር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተካሄደ።
አርባ ምንጭ፣ ሀምሌ 1/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተተገበረ ባለው የኢትዮጵያ የጎርፍ አደጋ አስተዳደር ፕሮጀክት ማዕቀፍ ውስጥ የተዘጋጀው በጎርፍ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት (Flood Early Warning System–FEWS) እና በተፋሰስ አስተዳደር ዙሪያ የመጀመሪያ ዙር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከሰኔ 23 እስከ 30/2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
የሥልጠናውን መርሃ ግብር የከፈቱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብደላ ከማል ሲሆኑ፣ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው በውሃ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችንና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በውሃ ሀብት አስተዳደርና በጎርፍ አደጋ ቅነሳ ላይ ያለው ትብብር ወደፊትም በበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሥልጠናው በሃይድሮሎጂ መረጃ አሰባሰብና ትንተና፣ በጎርፍ ትንበያ ሞዴሎች፣ በጎርፍ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት (FEWS)፣ በመረጃ አያያዝ፣ በመረጃ ትንተና እና ሪፖርት አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የተሳታፊዎችን ተግባራዊ ሙያዊ ብቃት በማጠናከር በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የውሃ ሀብት አስተዳደርና የጎርፍ አደጋ ቅነሳ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ያግዛል ብለዋል።
በሥልጠናው ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ክስተት ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ከአዋሽ ተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን እና ከሌሎች ተፋሰስ ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ 30 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ለአንድ ሳምንት በንድፈ ሐሳብና በመስክ ልምምድ የተደገፈው ሥልጠና ከሚኒስቴሩ የሥራ ተልዕኮ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በተቋማቸው በተግባር እንደሚያውሉ ገልጸዋል።
የሥልጠናው መርሃ ግብር በሰኔ 30/2018 ዓ.ም. በተካሄደ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የጎርፍ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር የጎርፍ አደጋን ለመቀነስና የማህበረሰብን መቋቋም አቅም ለማሳደግ ከአጋር ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር በቀጣይነት እያጠናከረ እንደሚቀጥል ገልጿል።