በአዋሽ ተፋሰስ ለሚገኙ ሴቶች በንግድና ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

በአዋሽ ተፋሰስ ለሚገኙ ሴቶች በንግድና ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

​ሰመራ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም በአፋር ክልል በአዋሽ ተፋሰስ የቤዚን አቀፍ የመቋቋም አቅም ማረጋገጫ በባዘርኔት ፕሮጀክት አማካኝነት በንግድና ሥራ ፈጠራ ዙሪያ የተዘጋጀ የሴቶች ሥልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

​በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሴቶችና ማኅበራዊ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የውብዳር አሚኖ በሀገሪቱ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ያላቸውን ሀብትና ንብረት እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ለማስገንዘብ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሥልጠናም ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ አመራሮች ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

​የሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም ​በያንጉዲ ራሳ አካባቢ ከሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ሴት ሰልጣኞች ሥልጠናውን በአካባቢያቸው ሰውና በገዛ ቋንቋቸው እንዲከታተሉ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

​የሥልጠናው ዓላማም ሴቶች በንግድና በሌሎች ገቢ በሚያስገቡ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እንዴት ወደ ሀብት መሸጋገር እንደሚችሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስገንዝበዋል።

​ወይዘሮ የውብዳር አሚኖ ሰልጣኞቹ በሥልጠናው ላይ በነጻነትና በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ በማቅረብ ሥልጠናውን በይፋ አስጀምረዋል።

በአፋር ክልል የአየር ንብረት ለውጥን የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠርና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሀንስ ዘሪሁን ገልጸዋል ።

ፕሮጀክቱ በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

​አስተባባሪው እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ዋና ዓላማውም የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ መፍጠር እና ማህበረሰቡ ወደ ተለያዩ የንግድ ስራ አማራጮች እንዲገባ በማድረግ የገቢ ምንጩን ማስፋፋት ነው።

ተፋሰሱ ሲለማ የግብርና ምርታማነት ከመጨመሩም በላይ አዳዲስ የንግድ እድሎች እንደሚፈጠሩ አክለው አስረድተዋል።

​ሴቶችን ያላሳተፈ የልማት ፕሮጀክት ግቡን ሊመታ አይችልም" ያሉት አቶ ዮሀንስ የመጀመሪያ ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ሴቶች በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት በዞን ስድስት ያንጉዲ ወረዳ ስር በሚገኙ ያንጉዲ እና ቴሪና ቀበሌዎች ለተውጣጡ 45 ሴቶች ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

​አካባቢው ደረቅ በመሆኑ የተፋሰስ ስራው ዋና ትኩረት ውሃን ማቀብ እንደሆነ የጠቀሱት አስተባባሪው በዚህም የአፈር እርጥበት እንዲጠበቅ፣ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲያገግም እና በገጸ ምድር ላይ የውሃ አማራጭ እንዲኖር በማድረግ ለሰው፣ ለእንስሳት እንዲሁም ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ጥበቃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

​በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየታዩ ያሉትን እንደ የንፋስ መጨመር፣ የዝናብ መቀነስ እና የሙቀት መጨመር ያሉ ተጽእኖዎችን ለመቋቋም የተፈጥሮ ሂደትን የተከተሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ውሃ በቀላሉ እንዳይተን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና በተፋሰስ እቅዱ አማካኝነት የሴቶችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የያንጉዲ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችውና በንግድ ስራ የምትተዳደረው ሀዊ ዋሊሊ ስልጠናው በተለይ ሴቶች ከአየር ፀባይ ጋር ያላቸውን ትስስር የሚገልጽ እና የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

ወ/ሮ ሀዋ በማል የተፋሰሱን ልማት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊም ተጠቃሚም ለመሆን የሚጠበቅብንን መወጣት ተፈጥሮን መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

ስልጠናው ለቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል አስተባባሪዎች ገልጸዋል ።

Share this Post