ኢትዮጵያን የሚመጥን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ የምዘና ስርዓት ያስፈልጋል። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ
ኢትዮጵያን የሚመጥን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ የምዘና ስርዓት ያስፈልጋል።
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ
ሰኔ 29/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያን የሚመጥን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ የምዘና ስርዓት ያስፈልጋል አሉ።
በሙያዊ ብቃት፣ ተአማኒነት እና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረቱ የብቃት ምዘና ጥያቄዎችን ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ፣ ከአርባምንጭ እና ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ምሁራን ጋር በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ውይይት ተደርጓል።
ክቡር ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት በተቋም አገልግሎት ለማግኘትና ጉዳይ ለማስፈፀም ተገቢ ያልሆነና መጉላላትን በመቀነስ የዜጎችን የመገልገል መብት ለማክበር ሪፎር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሰውም ሆነ ተቋም የሚቀረፀው በሚሰራው ስራ ልክ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ካልንበት የአሰራር ስርዓት በመሻገር የዜጎችን የመገልገል መብት ለማክበር በተቋሙ የተዘጋጀውን የሪፎርም ሲስተም ባለሙያው ተመዝኖ በቦታው ላይ እንዲቀመጥ፤ ተቋሙም አጥንትና ደም ተዋህደው የሚያምር ቁመና ኖሮት ዘመኑን ያማከለ አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆን እንዳለበትም አክለዋል።
የሚዘጋጁት ጥያቄዎች የሙያ ብቃትን በትክክል የሚለኩ፣ ግልፅ፣ ፍትሃዊ እና ዓለም አቀፍ የምዘና መርሆዎችን የተከተሉ እንዲሆኑ፤ በጥያቄ ዝግጅት ሂደትም የሚሳተፉ ምሁራንም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን፣ የመረጃ ምስጢራዊነትን እና የጥራት ማረጋገጫ መስፈርቶችን እንዲከተሉም አሳስበዋል።
በቀጣይ የሚከናወኑ የጥያቄ ዝግጅት፣ ግምገማ፣ ማረጋገጫ እና የመጨረሻ ማፅደቅ ሂደቶች በተቀናጀ እና በጥራት እንዲፈፀሙም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል።
የፊዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የተከበሩ ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ በበኩላቸው ሪፎርሙ ቢሮክራሲን በመስበር፣ አሰራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እና ብቁ መሪዎችንና ሠራተኞችን በማፍራት ተገልጋዮችን ከእንግልት ሊታደግ የሚያስችለውን ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የተወጠነ ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ነው ብለዋል።
ዘመናዊና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በተቋማት ውስጥ እውን ሲሆን የዜጎች እርካታ ይረጋገጣል፤ ውሳኔዎችም ፈጣንና ግልፅ ይሆናሉ ያሉት ዶ/ር መኩሪያ የአገልግሎት ስርዓቱን ለመቀየር ይቻላል፤ ይህንንም ለማድረግ የሰው አስተሳሰብና ብቃት ሊቀየር ይገባል ነው ያሉት።