በታችኘው አዋሽ አፈርን በመጠበቅ ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን በሚል መሪ ቃል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ።
በታችኘው አዋሽ አፈርን በመጠበቅ ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን በሚል መሪ ቃል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ።
ሰመራ፣ ሰኔ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. "አፈርን በመጠበቅ ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል በአዋሽ ተፋሰስ በያንጉዲ ከችመንት በባዘርኔት (Basernet) ፕሮጀክት የተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በይፋ ተጀምሮ በተሳካ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛል።
የልማት ንቅናቄው የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ፣ የከርሰ ምድር ውሃን ለማበልጸግ እና ዘላቂ የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ያሲን አሊ፣ የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን፣ የማሂ ረሱ ዞን አስተዳደር አመራሮች፣ የአዋሽ ተፋሰስ ባለሙያዎች፣ የያንጉዲ ወረዳ አመራሮች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ ሴቶችና ወጣቶች በሰፊው ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዕለቱ የተጀመረው ሥራም ለቀጣይ ውጤታማ አፈጻጸም ጠንካራ መሠረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ያሲን አሊ፣ የአፈርን ለምነት መጠበቅ የክልሉን ዘላቂ የምግብ ዋስትና፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ የጀመረውን ንቅናቄ በተከታታይነት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በያንጉዲ ወረዳ የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ሴቶችና ወጣቶችም ከፕሮጀክቱ ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች ጋር በመተባበር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን በከፍተኛ ተነሳሽነት በማከናወን ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ለማሻሻል፣ የውሃ ሀብትን ለማሳደግ እና የህብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።