በባዘርኔት ፕሮጀክት የዋቢሸበሌ ቤዚንን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በባዘርኔት ፕሮጀክት የዋቢሸበሌ ቤዚንን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ሀረር:- ሰኔ 25/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚያግዙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የባዘርኔት ፕሮጀክት/Basin Scale Resilience Initiative for Ethiopia/ የዋቢሸበሌ ቤዚንን ውጤታማ ለማድረግ በንግድና በስራ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሀመዲን ከቢር ሁሴን የኢንተርፕሩነርሺፕ እና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን (IWRM) በሚያግዝ መልኩ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ሴቶች በቤተሰብና በማህበረሰብ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያበረክቱት አስፈላጊ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል አስተዳዳሪው እንደዚህ ያሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የሴቶችን የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲያዳብሩ፣ የገቢ ምንጮቻቸውን እንዲያሰፉ እና በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብትና የውሃ ሀብት አስተዳደር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አክለዋል።

አቶ መሀመዲን ከቢር አክለውም የባቢሌ ወረዳ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የፕሮጀክቱ ብቸኛ ተጠቃሚ ወረዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ልዩ እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ተሳታፊዎች ስልጠናውን በንቃት እንዲሳተፉ፤ የሚያገኙትንም ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኢኮኖሚ እንዲያጠናክሩ እና በአካባቢያቸው የውሃና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ አርአያ እንዲሆኑ አክለው፤ ስልጠናው በተሳታፊዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የባቢሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ከሊፋ ገሪ ዩያ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ስልጠናው ለኢፋዲን ቀበሌ ነዋሪዎች በተለይም ለሴቶች የኢኮኖሚ አቅምን ለማጎልበትና የኑሮ ሁኔታቸውን ለማሻሻል ጥሩ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ከተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር /Integrated Water Resources Management/ ጋር በማያያዝ ሴቶች በውሃ፣ በአፈርና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በተፋሰስ ልማት፣ በውሃ አጠቃቀም ብቃት ማሻሻል፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በዘላቂ ልማት ሥራዎች ውስጥ የሚኖራቸው ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ከሊፋ አክለውም ስልጠናውን በትኩረት ተከታትለው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለማህበረሰባቸው ዘላቂ ጥቅም እንዲያመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ስልጠናው ለቀጣይ ሶስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ከምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ ኢብሮ ሳዴን ቀበሌ የተመረጡ ሴቶች እና ከወረዳው ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ፅ/ቤት ተሳትፈዋል።

Share this Post