የኃይል አቅርቦት ዘርፍን ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው።

የኃይል አቅርቦት ዘርፍን ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው።

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23/2018 (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ በቴክኒክ ድጋፍ የሚተገበረው ብሔራዊ የኤሌክሪፊኬሽን ፕሮገራም (NEP 3.0) በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ዘርፍን ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ላይ የዓለም ባንክ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የልማት አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻዎች የተሳተፉበት ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የኤሌክትሪክ ኃይል ለዕድገትና ለማንኛውም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ መሰረት በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ታዳሽ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ተደራሽነት የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ለብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር ትግበራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ ለማድረግ የኢነርጂ ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገ መሆኑንም የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በግሪድና ከግሪድ ውጪ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ጠቁመው፤ከመንግስት ተቋማት፣ ከልማት አጋሮችና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ደንበኞችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ በበኩላቸው ብሔራዊ የኤሌክሪፊኬሽን ፕሮገራም 1 እና 2 በሚተገበርበት ጊዜ የፋይናንስ እጥረት እና የውጪ ምንዛሪ ተግዳሮቶች እንደነበር ጠቁመው፤ ፍኖተ ካርታው በቀጣይ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 100% ለማድረስ ተቋማዊ ስትራቴጂ፣ የት አካባቢ፣ መቼ፣ እንዴት እና ምን አይነት ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

አቶ መስፍን አያይዘውም ብሔራዊ የኤሌክሪፊኬሽን ፕሮገራም (NEP 3.0) በ18 ቢሊዮን ዶላር የሚተገበር ሲሆን እ.ኤ.አ በ2035 ድረስ በሁሉም ኢትዮጵያ ክፍል እንደተጠቃሚው ፍላጎት የኃይል ተደራሽትን ለማረጋገጥ ወጪው በልማት አጋር የሚሸፈን ሲሆን መንግስትም ትልቁን ኢንቨስትመንት ይሸፍናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታን በማጠናቀር የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና በማሻሻል ኢንቨስትመንቶችን ያግዛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም 3.0 በቀጣይ 10 አመታት ውስጥ የሚተገብር ነው ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው የኤሌክትሪክ ኃይልን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ የታቅዶ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዓለም ባንክ የኢነርጂ ባለሙያ ወንድአየሁ ደምሴ በበኩላቸው ባንኩ በኢነርጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም በብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን እና በቀጣይም ድጋፉንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

Share this Post