የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመጠጥ ውኃ ጥራትና በአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ትብብር ሊጠናከር ነው።
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመጠጥ ውኃ ጥራትና በአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ትብብር ሊጠናከር ነው።
ሰኔ 23፣ 2026 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር የተከበሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ፣ አደጋና ቀውስ አስተዳደር ባለሥልጣን (NCEMA) ሰብሳቢ የሆኑትን የተከበሩ አሊ ሳኢድ አል ነያዲን (H.E. Ali Saeed Al Neyadi) በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
የክቡር አሊ ሳኢድ አል ነያዲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዓላማ በመጠጥ ውኃ ጥራት፣ በአደጋ ስጋት ቅነሳ እና በቴክኒክና ቴክኖሎጂ ትብብር ዘርፎች የጋራ የሥራ ማዕቀፎችን ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ወቅት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውኃ ጥራት ችግር፣ መንስኤዎቹንና መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎችን በዝርዝር አብራርተዋል።
በምላሹም የUAE ልዑካን ቡድን በሁለቱ አገራት መካከል በሚፈረም የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሰረት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ጉልህ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸው፣ ይህ አገራዊ እንቅስቃሴ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብትን በማሳደግ ለዘላቂ የውሃ ደህንነት ጠቃሚ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የUAE ልዑካን ቡድን በአፋር ክልል እና በአዳማ–ወንጂ አካባቢ የመስክ ምልከታ በማካሄድ የመጠጥ ውኃ ጥራት ችግሮችን በቀጥታ ተመልክቷል።
በምልከታው የተገኙ ግኝቶችን መነሻ በማድረግም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚታዩ የውኃ ጥራት ችግሮች ዘላቂ ቴክኒካዊ መፍትሔዎችን በጋራ ለማበልጸግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የUAE ልዑካን ቡድን የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቱን በማጠናቀቅ ወደ አገሩ ተመልሷል።