የባዘርኔት ፕሮጀክት በዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስኬት እያከናወነ ነው።

የባዘርኔት ፕሮጀክት በዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስኬት እያከናወነ ነው።

​ሰኔ 27/2018 ዓ.ም (ውኢሚ)፦የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት (BaSERINET) የዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ ፕሮጀክት ከአቅም ግንባታ እና ስልጠናዎች ጎን ለጎን፣ በኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ (catchment) ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ ያለው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለጸ።

​በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኢሊያስ ሁሴን እንደገለፁት፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ በሚገኘው የኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህ ተግባር ለሌሎች የባዘርኔት ፕሮጀክት ሥራዎች አጋዥና መሠረት የሚጥል መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው ዋና ዓላማውም የተጎዱ መሬቶችን በመልሶ ማልማት እና የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት በማስተዳደር የተፋሰስና የንዑስ ተፋሰስ አካባቢዎችን ማልማት ነውም ብለዋል።

​በማህበረሰብ ተሳትፎ የሚከናወኑ ቀጣይነት ያላቸው እነዚህ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች የረጅም ጊዜ ሥነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን እንደሚያስገኙ አቶ ኢሊያስ አብራርተዋል።

በዚህም ​የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የከርሰ ምድር ውሃን ለማሳደግ፣​የብዝሃ ሕይወትን መልሶ ለማጎልበትና የአፈር ለምነትን ለማሻሻል፣​የምግብና የሥነ-ምግብ ዋስትናን በማጠናከር በገጠር የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣​እንዲሁም ድህነትን ለመቀነስና ያለፈቃድ የሚደረግ ፍልሰትን ለማስቀረት አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል።

​ይህ የተፋሰስ ልማት ዘመቻ የብሄራዊ የባዘርኔት ቡድንን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ የህዝብ ንቅናቄ የመጣ ሲሆን፣ ከግንቦት 14/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከተፋሰስ የህብረተሰብ ማህበራት ጋር በተደረገ ውይይት፣ እቅድና አቅጣጫ መሠረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል ።

በንቅናቄውም የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የተፋሰስ ማህበራት፣ የልማት ሠራተኞች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና የመንግሥት አመራሮች በንቃት ተሳትፈዋል።

​በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 365 ወንዶች እና 240 ሴቶች በድምሩ 605 የአካባቢው ነዋሪዎች በተፋሰስ ማገገሚያ ሥራዎች ላይ በቀጥታ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

​የእነዚህ ሥራዎች ስኬታማ ጅምር የባለድርሻ አካላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት፣ ውጤታማ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና ስለ ዘላቂ ተፋሰስና ንዑስ ተፋሰስ አስተዳደር እየጨመረ የመጣውን ግንዛቤ የሚያሳይ መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በተያዘው እቅድ መሠረት የሚከናወኑ የተፋሰስ ማገገሚያ ግቦችን በላቀ ደረጃ ለማሳካት ጠንካራ መሠረት በመጣል፣ ለባዘርኔት ፕሮጀክት አጠቃላይ ዓላማዎች ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።

Share this Post