የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም (ው.ሚ.ኢ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደር ክብርት ኦሊቪያ ኦውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ሰፊ ውይይት አድርዋል።
የውይይታቸው ትኩረት የሁለቱን ሀገራት የውሃ፣ የኢነርጂና የዘርፉን አቅም ግንባታ የልማት ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነበር።
ክቡር ሚኒስትሩ እንግዶቹን በመቀበላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፎች ላይ በመስራት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሚደረገውን ጥረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአብነትም የኢነርጂ ልማት ዘርፍ 53 በመቶ ከግሪድ ሲሆን ቀሪው 10 በመቶ ከኦፍ ግሪድ በአጠቃላይ 63 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ይሁን ከሌላ የሚገኝን ሀይል ኢትዮጵያ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በጋራ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ጋር እያደረገች ያለው የሀይል ትስስር ማሳያ ነው ብለዋል።
ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያ በአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት የውሃ ሃብቷን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም ውጤታማ ስራ እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
መርሐ ግብሩ ለውሃ ሀብት መጨመርና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለተገኘው ውጤት ዕውቅና መስጠቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ሀገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታዘጋጅ መመረጧን ጠቅሰዋል።
ክብርት አምባሳደሯም ለተደረገላት አቀባበልና ገለፃ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ፤ ለአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
መርሐ ግብሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት ድንቅ ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የኢነርጂ ልማት ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።
ለሁሉም ትብብራዊ ስራዎች በቀጣይ ለመስራት የተቋሙን ስትራቴጂና ፎካል ሆኖ የሚገናኝ አንድ ሠው እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱም የራሱን ተወካይ ከስዊዘርላድ ተወካይ ጋር እንዲገናኙ ተደርጓል።
በውይይቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሌ እና ሌሎች መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።