ለችግር የማይበገር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰራተኛ ለመፍጠር በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስልጠና የጎላ ሚና ይጫወታል!

ለችግር የማይበገር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰራተኛ ለመፍጠር በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስልጠና የጎላ ሚና ይጫወታል!

ሐምሌ 9/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ)

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች በተሰማሩበት ሙያዊ ዘርፍ ራሳቸውንና ተቋሙን ለመለወጥ እንዲችሉና ለችግር አይበገሬ አስተሳሰብን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል በስራ ፈጠራና በሰራተኛ ማህበር ምስረታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ።

በዕለቱ በኢንተርፕርነርሺፕ ጽንሰ ሀሳብና እና በሽርክና ማህበር አደረጃጀት ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎች የቀረቡ ሲሆን በእነዚህ ስር የተካተቱ በርካታ ፍሬ ነገሮችን አስመልክቶ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።

የኢንተርፕርነርሺፕ ጽንሰ ሀሳብና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የስልጠና ሰነዱን ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሰራተኛውን የኑሮ ጫና ለመቀነስና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ሶስት እህት ማህበራት መኖራቸውንና እነዚህም የቁጠባና ብድር፣የሸማቾች ማህበርና የውሃና ኢነርጂ ሴቶች ማህበር ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረው እነዚህን ተቋማትም አጠናክሮ ማስቀጠልና ማሳደግ፣እንዲሁም ማስፋት ይገባል ብለዋል።

ከኢንተርፕርነርሺፕ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ማስገንዘብ ያስፈለገበትን ዋና ምክንያትም አቶ ኦልቀባ ሲገልጹ በተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥና ተነሳሽነት ፣ለማምጣትና የፋይናንስ የቁጠባ ባህልን ለማዳበር መሆኑን አስገንዝበዋል።

አያይዘውም በሰነዱ ላይ በመመርኮዝ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር፣ዓለም አቀፍዊና አገራዊ ሁኔታዎች፣የስራ ዕድል ፈጠራና ማህበራዊ ሀላፊነት፣የተግባር ቃል ኪዳንና ውሳኔ በሚሉ አርዕስቶች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማህበር ምስረታ ላይ ያተኮሩ ነጥቦች የተካተቱበትን የስልጠና ሰነድ ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ ሲሆኑ በመግቢያቸው ለችግር የማይበገር የውሃና ኢነርጂ አመራርና ሰራተኛ ለመፍጠር የአንድነት ማህበር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሰነዱም የማህበራት ምንነት፣መርሆዎች፣ተቋማዊ መዋቅር፣ የሚገኙ ጥቅሞችና ሀላፊነቶች፣የስነምግባር ደንብ መመሪያ፣ተግዳሮቶች፣ የአመሠራረት ቅደም ተከተል፣የቦርዱ ሚና፣ሃላፊነትና እንዲሁም የጥራት መመዘኛዎች ተካተው ቀርበዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች እንዲህ አይነት ስልጠናዎች በገንዘብ የሚወሰዱ ስልጠናዎች መሆናቸውን በመጠቆም የሰራተኛውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ መሰጠቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።

ከስልጠና አጀንዳዎች ጋር በተገናኘም ሰፊና ጠቃሚ ሀሳቦች በመድረኩ ላይ የተሰነዘሩ ሲሆን በአወያዮቹ በቂ ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ወደፊት ሁሉንም ሰራተኞች ባካተተ መልኩ ስልጠናው እንደሚሰጥ በመድረኩ ተገልጿል ።

Share this Post