3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የኢነርጂ ፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሯል

3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የኢነርጂ ፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሯል

ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የኢነርጂ ፈጠራ ስራዎቻቸውንና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ ልምድ ለመለዋወጥና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የሙያ ግንኙነት ለመፍጠር ዕድል እንደፈጠረላቸው በመድረኩ የተሳተፉ ባለሙያዎችና የፈጠራ ባለቤቶች ገለፁ።

በነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የኢነርጂ ኦዲት ባለሙያ ወ/ሮ አስኳል ተስፋዬ ተቋማቸው በኢነርጂና ነዳጅ ዘርፍ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልፀው፤ በኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ ብቃትን ለማሻሻልና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የኢነርጂ ኦዲት በማካሄድ ብክነት የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በመለየት ተገቢ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የምግብ ማብሰያ ምድጃዎች የጥራት ደረጃዎች እንዲያሟሉ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ደረጃውን የጠበቁ ምርቶች እንዲቀርቡ ጠቁመዋል።

ኤግዚቢሽኑ የተቋሙን ስራዎች ከማስተዋወቅ ባለፈ ህብረተሰቡ ስለ ኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ወ/ሮ አስኳል ገልፀዋል። ኢነርጂን በብቃት መጠቀምና መቆጠብ የገንዘብ ቁጠባን እንደሚያስገኝም አስረድተዋል።

የ2HF PLC መስራች አቶ ሄኖክ መልካም፣ በውሃና ኢነርጂ ሳምንት ላይ መሳተፉ የፈጠራ ስራውን ለማስተዋወቅና በሃይድሮጂን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሚሠሩ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ዕድል እንደሰጠው ተናግሯል።

አቶ ሄኖክ የተሽከርካሪዎችን የነዳጅ ፍጆታ ለመቀነስ የሚያግዝ የሃይድሮጂን ጄኔሬተር (HHO Generator) ቴክኖሎጂ ላይ ጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልፀው፤ መሳሪያው ውሃን በኤሌክትሮላይሲስ ሂደት ወደ ሃይድሮጂንና ኦክስጂን በመከፋፈል የሚያመነጭ ሲሆን፣ ሃይድሮጂኑን በነዳጅ ማቃጠያ ሂደት ውስጥ በተጨማሪነት ለመጠቀም የተዘጋጀ መሆኑን አብራርቷል።

መሳሪያው በተወሰኑ የሞተር ስርዓቶች ላይ በመግጠም የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ያለውን አቅም ለመፈተሽ እየተሠራበት ሲሆን ቴክኖሎጂው ከነዳጅ ፍጆታና ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ቅነሳ አንፃር ከ30 በመቶ በላይ ውጤት እንዳለው ገልፀዋል።

አቶ ሄኖክ አክለውም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በፈጠረልን ዕድል በሃይድሮጂን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር የሙያ ግንኙነት ለመመስረትና ለወደፊት የሚያግዙ የትብብር ዕድሎችን ለመፍጠር እንዳስቻላቸው አቶ ሄኖክ ገልፀዋል።

በአጠቃላይ 3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅ፣ በኢነርጂ ቁጠባና ብቃት ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት፣ ባለሙያዎችና የፈጠራ ባለቤቶች መካከል ትብብርን ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ ሆኗል።

Share this Post