ኢትዮጵያ የውሃ ደህንነትንና የWASH አገልግሎቶችን ለማሻሻል የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እያጠናከረች ነው

ኢትዮጵያ የውሃ ደህንነትንና የWASH አገልግሎቶችን ለማሻሻል የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እያጠናከረች ነው

ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በዘላቂነትና በተቀናጀ መንገድ በማስተዳደር የውሃ ደህንነትን ለማረጋገጥና የውሃ፣ የንፅህናና የመፀዳጃ አገልግሎቶችን (WASH) ለማሻሻል የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እያጠናከረች ነው።

"ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሰረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 16 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በሚካሄደው 3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ከሚነሱ ቁልፍ የውይይት ርዕሶች መካከል የውሃ፣ የንፅህናና የመፀዳጃ አገልግሎቶችን (WASH) አንዱ ነው።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የውሃ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ የውሃ ጥራትን ለመጠበቅና በተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ዘርፎች መካከል የተሻለ ቅንጅት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ስላለው ከWASH አገልግሎቶች ጋር ማቀናጀት ለህዝብ ጤና፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ያግዛል።

የውሃ ሀብቶችን በማልማት፣ በመንከባከብና ጥራቱን በመጠበቅ ለሁሉም ዘርፎችና ተጠቃሚዎች ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኙ የውሃ ምንጮችን መጠበቅ፣ የውሃ ጥራትን ማረጋገጥ፣ የንፅህናና የመፀዳጃ አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን መቋቋምም የውሃ ሀብት አስተዳደርን (IWRM) ትኩረቶች ናቸው።

በመርሀ ግብሩ ላይ WASH እና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን ወደ ተግባር ማሸጋገር፣ የተፋሰስ መረጃ አያያዝን ማዘመን፣ የውሃ ጥራትና የሃይድሮሎጂ መረጃዎችን በቴክኖሎጂ ማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ የውሃ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ የሳይንስና የፈጠራ መፍትሄዎችን ማሳደግም የመድረኩ ዓላማ ነው።

የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበርም የመንግስት ተቋማት፣ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና ማህበረሰቡ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ቢሆንም በዚህ ረገድ የሳይንሳዊ ጥናት ውጤቶችን ለፖሊሲ ውሳኔዎችና ለተግባራዊ ስራዎች ማዋል፣ የቴክኒክ አቅምን ማጠናከርና ለውሃ መሠረተ ልማት በቂ ፋይናንስ ማሰባሰብም ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ ተመላክቷል።

3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በWASH አገልግሎቶችና በዘላቂ ልማት ዙሪያ ያለውን የተቋማት ትብብር ለማጠናከር፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ወደ ተግባር ለመቀየርና ለውሃ ደህንነት የሚያበረክቱ ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማሳደግ ጠቃሚ መድረክ ነው።

Share this Post