የPRIM ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የ522.63ሚሊየን ዶላር የብድር ድጋፍ ተደረገ።

የPRIM ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የ522.63ሚሊየን ዶላር የብድር ድጋፍ ተደረገ።

ሚያዚያ 1/2016ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የPRIM ፕሮጀክትን (power sector Reform,Investment and Modernization in Ethiopia) ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የ522.63 ሚሊየን ዶላር የብድር ድጋፍ ከአለም ባንክ መገኘቱ ተገለጸ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ መንግስት በሀይል ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ስራ እየሠራ መሆኑንና በፈረንጆቹ 2030 ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ፕሮጀክቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

እንደብርሃን ለሁሉም ባሉ ፕሮጀክቶች የአለም ባንክ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የብድር ድጋፉ የሀይል ማሠራጫ መስመሮችን በማዘመን፣ በሀይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመር ላይ ያለውን ችግር በመቅረፍ፣ አዳዲስ የሀይል ማከፋፈያዎችን በመትከል፣ የከርሰ ምድር ሙቀትን በመጠቀም የጂኦ ተርማል ኢነርጅን በማስፋፋት እና አጠቃላይ የሀይል ሴክተሩን ለማዘመን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የኢነርጅና የነዳጅ ሴክተሮችን ተቋማዊ አቅም በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው የሚሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ አማካሪዎችን በመቅጠር፣ ጥናቶችንም ጭምር በማካሄድ ተቋማዊ የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ አላማ ያነገበ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙን ለየት የሚያደርገው የወለድ መጠኑ አነስተኛ መሆኑ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ልክም ውጤትን መሠረት ያደረገ ክፍያ ስለሚፈጸም ውጤታማ ለመሆን በሚያስችል መልኩ በየዘርፉ በፖሊሲ የታገዘ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

አክለውም ፕሮጀክቱ የሀይል ሴክተሩ ሪፎርምን ውጤታማ በማድረግ በማድረግ የኤሌክትሪክ ሀይል እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋሟት በሀይል ማመንጨትና ማስተላለፍ ተግባሩ የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።

Share this Post