በሃዋሳ ከተማ ለሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት (Faecal Sludge and Septage Treatmenet Plant ) ግንባታና ጥገና የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡

በሃዋሳ ከተማ ለሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት (Faecal Sludge and Septage Treatmenet Plant ) ግንባታና ጥገና የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡   ህዳር 23/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሃዋሳ ከተማ ለሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት (Faecal Sludge and Septage Treatmenet Plant ) ግንባታና ጥገና ከቻይናው CGCOC GROUP ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡   የውል ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከአለም ባንክ በተገኘ የብድር ድጋፍ በ23 ከተሞች የሚተገበር የሁለተኛው የከተሞች መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አካል የሆነው በሃዋሳ ከተማ የሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ እና ማስወገጃ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግስት ከተሞችን ጽዱ፣ ማራኪ እና ውብ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ያለሰለሰ ጥረት አጋዥ ነው ብለዋል፡፡   የፕሮጀክት ውሉን የወሰደው የቻይናው CGCOC GROUP ስራውን በሚገባ እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት በመግለጽ ከአሁን በፊት ያሳዩትን ጥንካሬ በዚህኛው ፕሮጀክት ላይም በሚገባ ተግባራዊ እንዲያደርጉና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አክለው ገልጸዋል፡፡     የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ቢሆንም የCGCOC GROUP ከተቀመጠው ጊዜ ቀድመው ስራውን እንደሚያጠናቅቁ በመተማመን ለዚህ ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡   የCGCOC GROUP ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ሊዩ ዊያንግ (Deputy General Manager Mr. Liu Weiqiang) ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በመጠጥ ውሃ፣ በነፋስ ሀይል፣ በብርጭቆ ፋብሪካና ሌሎች ፕሮጀክቶች በርካታ ውጤታማ ስራዎችን መስራቸውን ጠቅሰው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በገቡት ውል መሰረት ስራውን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡   የፕሮጀክት ግንባታ እና ጥገና ወጭው 262,753,655.91 ብር እንዲሁም 11,154,205.76 ዶላር መሆኑ በውል ስምምነቱ ተገልጿል፡፡

Share this Post