በቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ (BaSRINET) ፕሮጀክት ለአዋሽ እና ለዋቢሸበሌ ቤዚን የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት ስልጠና እየተሰጠ ነው።
አዳማ:- ጥር 04/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደርን የሚያሳልጡና በጣሊያን ትብብር የሚደገፈው ቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት (BaSRINET) ለአዋሽ እና ለዋቢሸበሌ ቤዚን የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት ላይ ለሚመለከታቸው የአዋሽና የዋቢሸበሌ ቤዚን ባለሞያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ስልጠናውን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የሚሰሩና ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎችን ለመተግበር በዕቅድ መመራት ስለሚያስፈልግ በተፋሰስ ልማት ዕቅድ አዘገጃጀት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በባዘርኔት ፕሮጀክት ፊዚካልና ባዮሎጂካል ስራዎች የሚመሩበትን ዕቅድ ለማዘጋጀት ቀደም ሲል ትኩረት የሚሹ ቦታዎችን የመምረጥና ወደስራ ለመግባት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደበበ የሚታቀደውን ዕቅድ እንዴት ወደ መሬት ማውረድ እንደሚቻልና ውሃን እንዴት ኦዲት ማድረግ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታዎችንም ማጤን ስሚገባ ባለሞያው በእጁ ያለውን መረጃ ለሌላው ማጋራት አለበት ብለዋል።
አቶ ደበበ አያይዘውም የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ለማዘጋጀት ስልጠናው ላይ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በክልልም ሆነ በዞን ደረጃ እንዴት ወደተግባር መቀየር ይቻላል የሚለውን በተከታታይ በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በዘላቂነት ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።
ብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ወሳኝ ስራዎችን ለመስራት የቤዚኖችን አቅም በመገንባ የሚያግዝ ነው ያሉት አቶ ደበበ ተፋሰሶችን በመምረጥና መረጃ በማደራጀት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልል ተሳታፊዎች ለተግባራዊነቱ ዕገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የውሃ፣ ኢነርጂ እና ኢንቬስትመንት ሴክተር ማናጀር Mr. Fabio Gaggi በበኩላቸው በባዘርኔት ፕሮጀክት በተከታታይ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና የመፈፀም አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመው፤ በንዑስ ተፋሰሶች ያዩትም ጅማሮ የሚበረታታ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ዶ/ር ብዙነህ አስፋው እና ዶ/ር ታዬ አለማየሁ የውሃ ሀብቱን በጋራ አልምቶ በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ዕቅድ ለማዘጋጀት የተፋሰስ ዕቅድ ምንነት፣ ሂደትና የሁኔታ ግምገማ (Situational Assessment) ላይ ገለፃ አድርገዋል።
በመድረኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ከክልል የፕሮጀክቱ አስፈፃሚዎችና የሚመለከታቸው ባለሞያዎች የተገኙ ሲሆን ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት ይቀጥላል።