በኢትዮጵያ 98 የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑ ተገለጸ።
የካቲት 13/2018ዓ .ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ 98 የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እያስገነባ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የአዴሌ (የብርሃን ተደራሽነት ለሁሉም) ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስ አለም መብራቱ ገለጹ።
ሰሞኑን በሱማሌ ክልል የተለያየ የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም ያላቸው 4 የሶላር ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በፕሮጀክቶቹ ይፋዊ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአዴሌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስዓለም መብራቱ በኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል የሶላር ሀይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት አንዱ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር በሁሉም ክልሎች ፍትሃዊነትን መሠረት ባደረገ መልኩ 98 የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ያሉት አስተባባሪው እስካሁንም 16 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
50 የሚሆኑት የሶላር ኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች ደግሞ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁና ቀሪዎቹ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት እስከ ሰድስት ወር ባለው ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ነው አስተባባሪው የገለጹት።
ፕሮጀክቶቹ ከአለም ባንክ በተገኘ የብድር ድጋፍ የሚገነቡ ናቸው ያሉት አስተባባሪው በዋናነት የገጠር አካባቢዎችንና ከዋናው የኤሌክትሪክ ሀይል ርቀው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበሩ ሲሆን በዚህ ሳምንት በሱማሌ ክልል ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች የዚሁ አካል ናቸው ብለዋል።
በሱማሌ ክልል 9 የሶላር ሀይል ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው ስድስቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
በዚሁ ክልል በዚህ ሳምንት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት የጋሻሞ ፣ የዲግ ፣የኑስትሪክና ምርቃን የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች በጥቅሉ 1.875 ሜጋ ዋት ሀይል የሚያመነጩ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ 949 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው ሲሆን የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ 10ሺህ 20 አባውራዎችን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ነው አስተባባሪው የጠቀሱት።
ከዚሁ ጎን ለጎን እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት በግለሰብ ደረጃ 140 ሺ የሚሆኑ ቤተሰቦችን እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ በሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
እንደ ሀገር 1400 የትምህርትና የጤና ተቋማትን የሶላር ሀይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በእቅድ ተይዞ በርካታ ሰራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
የሱማሌ ክልል ማእድን ኢነርጂና ነዳጅ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤድመን መሃመድ አሊ በበኩላቸው በሱማሌ ክልል ያሉ አብዛኛዎቹ ከተሞች አመሠራረታቸው በእጅጉ የተራራቀ በመሆኑ ከዋናው የሀይል መስመር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል የሶላር ሀይል ትልቅ አማራጭ ተደርጎ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
እንደክልል የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነት ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አሁን ላይ 14 ወረዳዎች ላይ እየተገነቡ ያሉ የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግልት ሲበቁ ሽፋኑ ወደ 60 በመቶ ከፍ ይላል ብለዋል።
እስካሁንም 6 የሶላር የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሠጡባቸው ባሉ አካባቢዎች ላይ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየተሻሻለ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለዚህ ደግሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና አጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አበርክቶ ያደረጉ አካላትን በእጅጉ አመስግነዋል።