ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   መጋቢት 21/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጋሞ ዞን ጋርዳማርታ ወረዳ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጎግሌ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጋሞ ዞን ጋርዳማርታ ወረዳ የጎግሌ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ500 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባና 6500 በላይ ቤተሰቦችን የሀይል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።   ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ታዳሽ ሀይልን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት መሠረት አሁን ላይ በአዴሌ ፕሮጀክት ብቻ ወደ 100 የሚጠጉ የሶላር ሚኒ-ግሪዶችን በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል። እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሀይል ተደራሽነትን 75 ከመቶ ለማድረስ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።   የጎግሌ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለትምህርት ተደራሽነት፣ ለጤና ተቋማት አገልግሎት፣ ለንግድ እና ለኢኮኖሚ እድገት መነሻ ሲሆን ለወጣቶች እና ለሴቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩበት ነውም ብለዋል። በአጠቃላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጋሞ ዞን ጋርዳማርታ ወረዳ የጎግሌ የጸለይ ሀይል ፕሮጀክት 700 ኪ.ዋ የማመንጨት አቅም ያለዉና ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ህብረተሰቡን ሀይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።   ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በመጨረሻም ህብረተሰቡ ፕሮጀክቱ የታለመለትን አገልግሎት እንዲሰጥ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቀው አደራ ብለዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ክቡር ዶ/ር ቦሾ ቦንጌ፣ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች በፕሮጀክቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

Share this Post