ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የአቅም ግንባታ ስልጠና ውል ስምምነት ተደረገ፡፡

ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የአቅም ግንባታ ስልጠና ውል ስምምነት ተደረገ፡፡ ህዳር 17/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለ56 ከተሞች ከውሃ አገልግሎት ተቋማት ለተውጣጡ ባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ውል ስምምነት ተደረገ፡፡   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በገጠርና በከተማ በተለያዩ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራው የአቅም ግንባታ ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለብዙ አመታት ያካበተውን አቅም በመጠቀም ብቃት ያላቸውን ባለሞያዎችን ለማፍራት ስትራጂ ነድፈን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ብለዋል፡፡   ሚኒስቴር መ/ቤቱ በመንግስትና በአጋር አካላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የአቅም ግንባታ ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ክቡር አምባሳደር ለብዙ አመታት ያካበተውን የአቅም ግንባታ ስልጠና ልምድ ተጠቅሞ ወደ ተግባር በመለወጥና በተመረጡ የስልጠና ሞጁሎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ድጋፍ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡ ክቡር አምባሳደር አክለውም ስራውም የተሳካ እንዲሆን የከተሞች የውሃ አገልግሎቶችን አቅም በማጠናከር በቢሮዎች፣ በወረዳዎችና በሚኒስቴር መ/ቤታችን የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች በጋራ ሆነው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   በተለይ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ውስጣዊ አቅምን ከማጎልበት አንፃር አገር በቀል እውቀትንም ወደተግባር በመቀየር ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል ኢንስቲትዩቱ ተጠናክሮ ወደ ስራ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለተቋሙ የሚያደርገው ይህ ነው የማይባል ድጋፍ እያመሰገንኩ የሚሰጠው ስልጠና በትክክል ዓላማውን አሳክቷል ወይ የሚለውንም በክትትልና ድጋፍ ውጤታማ ስራ ሰንተን ስኬታማ እንሆናለን ብለዋል፡፡   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዶጊሶ ጎና በበኩላቸው ስምምነቱ ከሁሉም ክልሎች ለ56 ትናንሽና መካከለኛ ከተሞች ከውሃ አገልግሎት ተቋማት ለተውጣጡ የቴክኒክ፤ የፋይናንስና የዕቅድ ባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ከተሰጠ በኃላ ስልጠናው ውጤታማ ስለመሆኑ በስራቸው ላይ ክትትልና ድጋፍም ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከተሞቹ በውሃ ልማት ፈንድ የረጅም ጊዜ ብድር ያገኙና የውሃ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት በመሆናቸው ብድሩን ለመመለስ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ብድራቸው በጊዜ ገደብና በአግባቡ እንዲመልሱ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና መሆኑንም ገልፀዋል፡፡   ከዚህ በፊትም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ብድራቸውን በወቅቱ እንዲመልሱ ስልጠና ይሰጣል፤ በቁሳቁስ እንደግፋለን፤ በአካልም ተገኝተንም እንደግፋለን ያሉት አቶ ዶጊሶ ስምምነቱ በ56 ከተሞች በሚቀጥሉት 18 ወራት የሚጠናቀቅና ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት /AFD/ በተገኘ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በ48,725,761.05 በሆነ ወጪ የሚተገበር ሲሆን በአሰልጣኙ ተቋም በኩል ክትትል እየተደረገ ከተሞችን የማብቃት ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡

Share this Post