ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የፀሓይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የፀሓይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   መጋቢት 23/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ)የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በሳላማጎ ወረዳ ያስገናባቸውና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገገበት የዶሜ ገሮ የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ዛሬ ያሰመረቅነው ፕሮጀክት ከ400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት እና ከ6ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡   ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማከል በጣም ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ በአደሌ ፕሮጀክት ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር በክልሉ ለመገንባት ከታሰቡት ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ዛሬ ያስመረቅናቸውን ጨምሮ ሰባት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።   ፕሮጀክቶቹ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል። በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው የአካባቢው ማህበረሰብ ፕሮጀክቱን እንደራሱ ንብረት አድርጎ ሊጠብቅ ይገባል በማለት መልክት አስተላልፈዋል።   ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው ተቋሙ የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ 7 የፀሀይ ሀይል ማመንጫዎች ገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡   የአካባቢውን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባው ፕሮጀክት 625 ኪ.ዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ያላለውና ለ20አመት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በመሆኑም ገልጸዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Share this Post