ከ2.72 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለከርሰምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታ የሚውል የ49 ጥልቅ ጉድጔድ ቁፋሮ ዉል ስምምነት ተደረገ።

ከ2.72 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለከርሰምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታ የሚውል የ49 ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ዉል ስምምነት ተደረገ።   ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (ው.ሚ.ኢ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተተገበረ የሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ2.72 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለከርሰምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታ ጥናት ጉድጓድ ለማስቆፈር ውል ስምምነት ተደርጓል።   በስምምነት ፊርማው ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ፕሮጀክቱ እንደ ተቋም ትልቅ ስኬት በመሆኑ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመመለስ አለኝታውን ቀድሞ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሠው ሥራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራና የማማከር ስራውን በሚገባ በማከናወን ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።   ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም የውሀ መጠንና ጥራት ለመለካት የሚካሄድ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራው ለአካባቢው አርብቶአደር ዘለቀታ ያለውና የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ ታሳቢ ተደርጎ የተቀረፀ ፕሮጀክት በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበትና ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡   በፕሮጀክቱ 49 የከርሰ ምድር የውሃ ጥናት ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ የሚካሄድ ሲሆን እያንዳንዱ ከ500 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው መሆኑን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አብራርተዋል፡፡   አክለውም ክቡር አቶ ሞቱማ ከ8 ኮንትራክተሮች ጋር የተወሰደው የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ልየታ ጉድጓድ ቁፋሮ የውል ስምምነት ዋንኛ ዓላማው ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድር ውሃ መጠን በማጥናትና በማወቅ ጉድጓዶችን መፈተሽ /test wells/ መሆኑንም አፅእኖት ሰተው ገልፀዋል፡፡   ኮንትራቱን የፈረሙት አማካሪዎችና ኮንትራክተሮችም ከተቋሙ ጋር መስራት ጥሩ ዕድል መሆኑን ገልፀው፤ ሌተቀን በጥራትና በፍጥነት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ከርሠ ምድር ልማት ፕሮጀክት ከአለም ባንክ በተገኘ 210 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ /grant/ የሚሠራ ሲሆን ዛሬ የተፈረመው የ2.723,555,671 ቢሊዬን ብር የከርሠ ምድር ጥናት ቊፋሮ የዚሁ አካል ሲሆን ቁፋሮውም በሱማሌ፣ ብላቴ፣ በአሳሳ፣ በቦቆጂ፣ በአጣዬ፣ በላይኛው ወይጦ እና በላይኛው ኦሞ አካባቢ የሚከናወን ሲሆን በውሉ መሰረት በ240 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

Share this Post