ከ1500 በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ከ1500 በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   መጋቢት20/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ መጫ ቀበሌ ከ1500 በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ መጫ ቀበሌ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባና ከ1500 በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።   ኢነርጂ ለማንኛውም እንቅስቃሴ ምትክ የሌለው ቁልፍ ግብአት ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ሀገራችን ደግሞ እምቅ የታጃሽ ሀይል ሀብት ባለቤት ብትሆንም እስከ ከሁን ጥቅም ላይ ማዋል የቻለችው ጥቂቱን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል ። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ታዳሽ ሀይልን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት መሠረት አሁን ላይ በአዴሌ ፕሮጀክት ብቻ ወደ 100 የሚጠጉ የሶላር ሚኒ-ግሪዶችን በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።   እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሀይል ተደራሽነትን 75 ከመቶ ለማድረስ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 10 የሶላር ሀይል ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ማብቃታችን ማሳያ ነው ብለዋል። የሶላር ሀይልን ስንጠቀም የበካይ ጋዝ ልቀትን ከመቀነስ አኳያ የምናበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በካርበን ፋይናንስ ተጠቃሚ እንሆናለንም ብለዋል።   በአጠቃላይ በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ መጫ ቀበሌ የሶላር ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ለህብረተሰቡ ሀይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመግለጽ የህብረተሰቡ ፕሮጀክቱ የታለመለትን አገልግሎት እንዲሰጥ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቀው አደራ ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ለፕሮጀክቱ ትግበራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የክልሉን መንግስት አመስግነዋል።   በመርሀ ግብሩ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላይ ፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ አቶ መላኩ በላይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች በፕሮጀክቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

Share this Post