ከ10.3 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የክትትል ፣ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ውል ተፈረመ።
መጋቢት 1/2017ዓ.ም አዲስ አበባ (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ10.3 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የክትትል ፣ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ውል ተፈራረመ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዋን ዋሽ ፕሮግራም ሲአር ዋሽ ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ የአጋም በር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን የክትትል፣ ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ስራ እንዲያከናውኑ ከላሊ በላ ጥናት ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ድርጅት ጋር ውል ተወስዷል።
የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የአጋም በር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ውጤታማ በሆነ መልኩ ተገንብቶ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ተገቢ የሆነ የቁጥጥር ፣ክትትል እና የኮንትራት አስተዳደር ስራ እንዲሰራ የተደረገ የውል ስምምነት ነው ብለዋል።
ከ10.3 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበትን የቁጥጥር ፣ክትትል እና የኮንትራት አስተዳደር ስራ የሚያከናውነው ድርጅቱ ከአሁን በፊት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ጥሩ ስራ የሰራ ሲሆን በሚፈለገው የቁጥጥር ደረጃ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ስራውን በመከታተል በታለመለት ጊዜ እና ጥራት እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የላሊ በላ ጥናት ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ፍስሃ ወንዲፍራው በበኩላቸው ከአሁን በፊት በሰባት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በሰሯቸው ስራዎች ጥሩ አፈጻጸም እንደነበራቸው ገልጸው ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ተገቢውን ዝግጅት አድርገው እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።
በገቡት ውለታ መሠረትም በተሻለ ጥራት እና በተቀመጠው ጊዜ ስራውን ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል።
ፕሮጀክቱ በአስራ ስምንት ወራት እንደሚጠናቀቅም በውል ስምምነቱ ተገልጿል።