ታዳሽ ኃይልን ከግብርና እና ከምግብ ዋስትና ጋር የሚያስተሳስሩ ሳይንሳዊ ጥናቶች ቀረቡ

ታዳሽ ኃይልን ከግብርና እና ከምግብ ዋስትና ጋር የሚያስተሳስሩ ሳይንሳዊ ጥናቶች ቀረቡ

አዲስ አበባ — ጥቅምት 19 ቀን 2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)-በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም “ለወደፊት የውሃ እና ኢነርጂ አስተማማኝነት አጋርነት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት፤ ታዳሽ ኃይልን ከዘመናዊ ግብርና እና ከምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ስልቶች ጋር በቀጥታ የሚያገናኙ አበይት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደረገባቸው።

በመድረኩ ላይ የቀረቡት ጥናቶች በሙሉ ውሃ፣ ኢነርጂ እና የአየር ንብረት ለውጥ እርስ በርሳቸው ፍጹም የማይነጣጠሉና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን በምክንያትና በማስረጃ ያረጋገጡ ናቸው።

በመድረኩ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ጥናት የታዳሽ ኃይል የፀሐይ ብርሃን በጫጩቶች ማሳደግ አፈጻጸም ላይ ያለው ተፅዕኖ የሚል ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ መስመር ባልደረሰባቸው የገጠር ቀጠናዎች ውስጥ ታዳሽ የሶላር ቴክኖሎጂን ከዶሮ እርባታ ጋር ማቀናጀት ያለውን ፋይዳ በተጨባጭ አስገንዝቧል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ጭስ አልባ በሆኑ የሶላር የሙቀት ማመንጫዎች እና መብራቶች መጠቀም የጫጩቶችን የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ እና የዶሮዎችን የእድገት አፈጻጸም በማሳደግ የገጠር አርሶ አደሮችን ከተረጂነት ወደ ዘላቂ ምርታማነት የሚያሸጋግር መሆኑ ተረጋግጧል።

ከዚሁ ተከትሎ የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የታዳሽ ቴክኖሎጂዎች ምርታማ አጠቃቀም ላይ የተደረገ ክለሳ እና አንዳንድ ማረጋገጫዎች የሚል ሲሆን፤ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል ጸጋ ከምርት ጋር ማገናኘት ያለውን ጠቀሜታ በ አብራርቷል ።

ይህ አሰራር አርሶ አደሮች ከአየር ንብረት መዛባትና ከናፍጣ ጄኔሬተር ጥገኝነት ወጥተው የምርት መጠናቸውን ከማሳደግ ባለፈ አገራዊ የምግብ ዋስትናን በተሟላ ሁኔታ እንዲገነቡ ማድረግ እንደሚያስችል ተመልክቷል።

በተያያዥነት ትኩረት የተሰጠው ጥናት ደግሞ የተቀናጀ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን፣ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች እና ባዮጋዝ በኢትዮጵያ የገጠር እና የልማት ምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማፋጠን በሚል ርዕስ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ይህ ጥናት የገጠር መብራትን፣ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን እና ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ማቀናጀት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና እና የምግብ ስርዓት ሽግግርን ለመፍጠር ያለውን ወሳኝ ሚና በዝርዝር አሳይቷል።

በመድረኩ ላይ የቀረቡት ጥናቶች ውሃ፣ ኢነርጂና የአየር ንብረት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ተገንዝቦ ታዳሽ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን ከግብርና ምርታማነትና ከምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ስልቶች ጋር በላቀ ሁኔታ ማቀናጀት የዘርፉን ስኬት ወደ መሬት ለማውረድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።

Share this Post