የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን የተማሪዎችን የዕውቀት አድማስ አስፍቷል።
የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን የተማሪዎችን የዕውቀት አድማስ አስፍቷል።
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 18/2019ዓ.ም
የሦስተኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት አካል የሆነውን ኤግዚቢሽን የጎበኙ ተማሪዎች፣ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የተመዘገቡ የቴክኖሎጂ እድገቶችን ለመረዳትና ስለ ሀገሪቱ የውሃና ኢነርጂ ሀብቶች ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እድሉ እንደረዳቸው ገለጹ።
የቡርቃዩ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኮኬት መንግስቱ፣ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የታዩት ዘመናዊ አሠራሮችና የቴክኖሎጂ እድገቶች እንዳስደነቁት ጠቅሷል።
በተለይም የኒውክሌር ኢነርጂን ጨምሮ በኢነርጂ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ስለ ዘርፉ ያለውን ግንዛቤ እንዳሰፉለት አስረድቷል።
ውሃ ለሕይወትና ለልማት ወሳኝ ሀብት በመሆኑ በቁጠባ መጠቀምና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የገለጸው ተማሪው፣ ወጣቶችም በዘርፉ ልማት ላይ ተነሳሽነትና ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ሌላኛዋ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናናቲ ነገራ በበኩሏ፣ ኤግዚቢሽኑን በመጎብኘቷ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ስለተሠሩ ሥራዎች፣ ስለ ቴክኖሎጂ እድገትና ስለተመዘገቡ ለውጦች ብዙ ነገር ለመማር እንደቻለች ተናግራለች።
ያለንን የውሃና ኢነርጂ ሀብት በቁጠባና በአግባቡ በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የጠቆመችው ተማሪዋ፣ በዘርፉ ላይ ሚኒስቴሩ እየሠራ ያለውን ሥራም አድንቃለች።
በተለይም ወጣቶችና ሴት ተማሪዎች እውቀትን በሚያሳድጉ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግንዛቤን በሚያሰፉ እንዲሁም ስለ ሀገራቸው ሀብት ያላቸውን ንቃተ ህሊና በሚያጎለብቱ ኤግዚቢሽኖች ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ መክራለች።
ፊዚክስን እንደሚወድ የገለጸው የ11ኛ ክፍል ተማሪ አልፋ ሙሉቀንም፣ ኤግዚቢሽኑ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ያለውን እውቀት ለማስፋት እንደረዳው ገልጿል።
በተለይም ኢነርጂ ለምርታማነት ማደግና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ያለውን አስተዋጽኦ በተሻለ ሁኔታ እንደተረዳ አብራርቷል።
ተማሪዎች ከኤግዚቢሽኑ ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ለራሳቸው እድገትና ለሀገራቸው ልማት እንዲያውሉ መልዕክት ያስተላለፈው ተማሪው፣ እንደዚህ ያሉ የትምህርትና የልምድ ልውውጥ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁሟል።
የተማሪዎቹ አስተያየት እንደሚያመለክተው፣ ኤግዚቢሽኑ የውሃና ኢነርጂ ዘርፎችን ለሕዝብ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ለማስተዋወቅ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፍላጎትን ለማነሳሳት፣ የሀብት ጥበቃ ባህልን ለማጠናከርና ወጣቶች በሀገራዊ ልማት ያላቸውን ሚና እንዲገነዘቡ ለማገዝ ያለውን አስፈላጊነት ያሳያል።
በመሆኑም እንደዚህ ያሉ ኤግዚቢሽኖች የተማሪዎችን የተግባር ትምህርት ከክፍል ውስጥ እውቀት ጋር በማገናኘት፣ የፈጠራ አቅማቸውን በማበረታታትና ለወደፊት የሳይንስ፣ የኢንጂነሪንግና የቴክኖሎጂ ዘርፎች ባለሙያዎች እንዲሆኑ ፍላጎታቸውን በማጎልበት ወሳኝ ሚና አላቸው።