በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እየተሠሩ ስላሉ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች አዲስ ግንዛቤ እንዳገኙ ተማሪዎች ገለጹ።
በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እየተሠሩ ስላሉ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች አዲስ ግንዛቤ እንዳገኙ ተማሪዎች ገለጹ።
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 17/2019ዓ.ም
በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የተካሄደውን የሦስተኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን የጎበኙ ተማሪዎች፣ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እየተሠሩ ስላሉ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች አዲስ ግንዛቤ እንዳገኙ ገለጹ።
በኤግዚቢሽኑ ላይ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ ተማሪዎችና የቡርቃ ኖኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመገኘት የውሃና ኢነርጂ ዘርፎችን በተመለከተ እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተመልክተዋል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ኖላዊት ወልዳይ፣ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የሚወጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ጠቁማለች።
ኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል እየሠራች ያለችውን ሥራና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ አሠራሮችን መመልከቷ እንዳስደሰታት ገልጻለች።
ውሃ ለሕይወትና ለልማት ወሳኝ ሀብት በመሆኑ እንደ ተራ ነገር መቆጠር እንደሌለበት የገለጸችው ተማሪዋ፣ ውሃን ከምንጩ አንስቶ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ከብክለትና ከብክነት መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝባለች።
በተመሳሳይ፣ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ዘገብርኤል ላከ፣ በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ኤግዚቢሽን መሳተፉ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተግባር ለመመልከትና ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደፈጠረለት ተናግሯል።
ተማሪው በጉብኝቱ የተለያዩ የውሃ ቴክኖሎጂዎችን መመልከቱን፣ የተበከለ ውሃን በማከም መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልባቸውን መንገዶችም መረዳቱን ገልጿል።
በኤግዚቢሽኑ የተመለከታቸው የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያስመዘገበች ያለችውን የልማት ውጤት የሚያሳዩ መሆናቸውንም አስረድቷል።
ወጣቶች በማንበብ፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር እውቀታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የጠቆመው ተማሪው፣ እንደዚህ ያሉ የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሚቀርቡባቸው ኤግዚቢሽኖች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
በዕለቱ የቡርቃ ኖኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ኤግዚቢሽኑን ጎብኝተዋል።
የሦስተኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን በዘርፎቹ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና የምርምር ውጤቶችን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግንዛቤን ለማሳደግና በተለይም የወጣቶችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማነቃቃት የሚያግዝ መድረክ ነው።