የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የሥራ ማስጀመሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የሥራ ማስጀመሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ መስከረም 20/2019 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) — በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት (BaSERNET) በጣሊያን የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፣የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች በትብብር፣ በተጠያቂነትና በግልጽ ግንኙነት መሥራት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ የሥራ ማስጀመሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ። መድረኩ ከፕሮጀክቱ ውል ወስደው ወደ ሥራ የገቡና ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ ኮንትራክተሮችን፣ አማካሪዎችን፣ አቅራቢዎችንና ሌሎች ተሳታፊዎችን አሳትፏል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ መድረኩ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ወቅት የሚያስፈልጉ ውሳኔዎችን በጋራ ለመለየት፣ እንቅፋቶችን ቀድሞ ለመለየትና ለመፍታት እንዲሁም የተሳታፊዎችን የሥራ ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። የIFAD የቴክኒክ ባለሙያ ዶ/ር ኤሊያስ ተድላ በሰጡት ሥልጠና፣ የልማት ፕሮጀክቶች በድጋፍ በሚገኝ ሀብት የሚተገበሩ በመሆናቸው ሀብቱን በአግባቡ በመጠቀም ለማህበረሰቡ ተጨባጭና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሥልጠናው የፕሮጀክቱ መሠረታዊ ዓላማዎች፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ፣ የዓለም አቀፍ የልማት ፕሮጀክቶች ባህሪያት፣ የፕሮጀክት መዘግየት ምክንያቶችና መዘግየትን ለመከላከል የተሳታፊዎች ድርሻ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ገለጻና ውይይት ተካሂዷል። በተጨማሪም የፕሮጀክቱ ሥራ ውጤት ተኮር ብቻ ሳይሆን፣ በማህበረሰቡና በአካባቢው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያስከትል በጥንቃቄ መተግበር፣ችግሮችንም ከመከሰታቸው በፊት በመለየትና በመቆጣጠር ቅድመ ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር መከተል እንዳለበት ተጠቁሟል። ከአማካሪዎች፣ ከአቅራቢዎችና ከኮንትራክተሮች የሚጠበቁ ኃላፊነቶችም ተብራርተዋል። ለተሰጠ ሥራ ባለቤትነትን መውሰድ፣ በጊዜ፣ በጥራትና በወጪ ተጠያቂነትን መጠበቅ፣ ችግሮችን በወቅቱ መለየትና መፍትሔ መፈለግ፣ ትብብርን ማጠናከርና ግልጽ ግንኙነትን መፍጠር ከዋና ዋና የሥራ መርሆዎች መካከል ተጠቅሰዋል። ተሳታፊዎችም በሥራ ላይ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ችግሮችና በሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ላይ ሃሳቦቻቸውን በማካፈል፣በ2019 ዓ.ም. የተሻለ የፕሮጀክት አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያግዙ የመፍትሔ አማራጮችን በማቅረብ የየራሳቸውን ኃላፊነት በተገቢው በመወጣት፣በትብብርና በግልጽ ግንኙነት በመሥራት ለተሻለ የፕሮጀክት አፈጻጸም እንደሚያስመዘግቡ አጠናክረዋል፡፡ ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikto  

Share this Post