የውሃ ፍቃድ አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል የቴክኒካል አቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የውሃ ፍቃድ አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል የቴክኒካል አቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።   መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል በጋራ የሚተገበረው የBRIGHT ፕሮጀክት የኤሌክትሮኒክ ውሃ ፍቃድ ስርዓቱን (e-permit) ለማዘመን የሚያስችል የቴክኒካል አቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግና የወረቀት ስራዎችን በማስቀረት ተገልጋዮችን ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ስልጠናውን በይፋ ሲያስጀምሩ ለውሃ ፈቃድ አሰጣጥ የe-Service ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ሲሆን፤ ባህላዊና በወረቀት ላይ የተመሰረተ የውሃ ፍቃድ አሰጣጥን ወደ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ግልፀኝነት ያለው ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ቴክኖሎጂው የአገልግሎት ጥራትን ይጨምራል፤ ፈጣን እና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥንም ያሻሽላል ብለዋል።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ የውሃ ፍቃድ አጠቃቀም ዴስክ ኃላፊ አቶ ጨመዳ ቶሊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ከሚሰራቸው ዋና ዋና ስራዎች መካከል የውሃ አጠቃቀም በፍቃድ እንዲመራ ማድረግ ሲሆን፤ ቀድሞ በማንዋል ሲሰራ የነበረው አሰራር ተጠቃሚዎችን ተደራሽ የማያደርግ በመሆኑና የ e-Service ቴክኖሎጂ አማራጭ መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ በBRIGHT ፕሮጀክት የቴክኒካል ስልጠና ተዘጋጅቷል ብለዋል።   ማንኛውም የውሃ ተጠቃሚ ፍቃድ ሊኖረው ይገባል ያሉት አቶ ጨመዳ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የውሃ ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በቀጣይ ለተጠቃሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል። በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል የBRIGHT ፕሮጀክት የውሃ ልማት አስተዳደር (WRM) ቴማቲክ የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች አስተባባሪ ዶ/ር አደይ ንጋቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የውሃ ፍቃድ አሰጣጥ ቀድሞ በወረቀት ሲሰራ የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ የኤሌክትሮኒክ የውሃ ፍቃድ አሰጣጥ በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመቀየር ዲጅታላይዝ ለማድረግና የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ያለመ ስልጠና ነው ብለዋል።   ዶ/ር አደይ አክለውም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለማውን ሲስተም የአገልግሎት ስርዓትን ለማሻሻል፣ የተጠቃሚዎችን እንግልት ለመቀነስና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሲስተሙን ለሚያስተዳድሩ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የአይቲና የሚመለከታቸው ዴስክ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው ፅ/ቤቶች የቴክኒካል አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ነው ብለዋል።   እንደሀገር የውሃ ፍቃድ አስተዳደር አጠቃላይ እይታ ምን እንደሚመስል ከስልጠናው በፊት በተቋሙ ባለሙያ የቀረበ ሲሆን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለማው ሲስተም PERAGO ከተባለ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለሙያዎች ስልጠናው በሚሰጡበት ወቅት የውሃ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን ለማዘመን ብሎም ሰርቪሱን ከማሻሻል አንፃር ለተጠቃሚው የታሰበ ቢሆንም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቤዚን ፅ/ቤቶችን ጨምሮ እንደተቆጣጣሪ አካል የሚያስተዳድሩ ስለሆነ ተጠቃሚው እንዴት መጠቀም እንደሚችል ለማስገንዘብም ያግዛል ብለዋል።

Share this Post