የውሃ ሀብትን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል በዕቅድ መመራት ያስፈልጋል ተባለ።
መጋቢት/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃ ሀብት መረጃን ለማስተዳደርና ለማጋራት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲካሄድ የነበረው የውይይት ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የውሃ ሀብትን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል በዕቅድ መመራት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።
በማጠቃለያ መርሃግብሩ ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል (WLRC) ጋር የሚተገበረው የBRIGHT ፕሮጀክት የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በውይይቱ የተገኘውን ግብዓት በማጠናከር የተሻለ፣ የሚያሰራና ተቀባይነት ያለው መመሪያ እንዲሆን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
በቀጣይ ከየሴክተሩ የተነሱትን ሃሳብና አስተያየቶች በማሰባሰብ መመሪያውን በማዳበር፤ ለበላይ ኃላፊዎች ከመቅረቡ በፊት የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች የጋራ ሊያደርጉት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ክቡር አቶ ሞቱማ አያይዘውም መመሪያው ለውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች ገዢ ስለሆነ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንም ለመፍታት ያግዛልም ብለዋል።
የብራይት ፕሮጀክት አገር አቀፍ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው በኔዘርላንድና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው የብራይት ፕሮጀክት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በሀገራችን ለማስፈንና በተፋሰሶች ላይ ትግበራ ለማካሄድ ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ይሰራል ብለዋል።
ለውሃ ሀብት አስተዳደር ወሳኝ የሆነውን የውሃ ሀብት መረጃ እንዴት ማስተዳደርና ማጋራት ይቻላል፤ በህግ ማዕቀፍ የተዘጋጀውም ዶክመንት በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለው ላይ በመወያየት የውሃ ሀብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል መረጃዎችን ማስተዳደር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ማማሩ በዕቅድ ለመመራትም መረጃ ወሳኝ ነው ብለዋል።