የውሃ ሃብት መረጃን ለማስተዳደርና ለማጋራት በሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ የምክክር አውደ ጥናት ተካሄደ።
መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ልማት ማዕከል ጋር በጋራ የሚተገበረው የBRIGHT ፕሮጀክት የውሃ ሃብት መረጃን ለማስተዳደርና ለማጋራት በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ የምክክር አውደ ጥናት ተካሄደ።
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የውሃ ሀብት አስተዳደር በተቋሙ ላሉ ለመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እና ለኢነርጂው ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ለመሳሰሉት ትላልቅ ግድቦች የውሃ ሀብት መረጃ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በዘርፉ ለምንሰራቸው ስራዎች ተገቢ መረጃ ካለን ወጪን፣ ጥራትንና ጊዜን ያማከለና እንደ ህዳሴው ግድብ ለሌሎች ምሳሌ የምንሆንበት ልማት ለማልማት፤ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ያሉትን መረጃዎች በጥራት ማደራጀት ይገባልም ብለዋል።
የውሃና መሬት ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ሲያስተላልፉ ውሃ ቀጣይነት ላለው ልማት ወሳኝ በመሆኑ በውሃነክ ጉዳዮች ላይ ያሉ መረጃዎችን በማደራጀትና በማዘመን ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተደራሽ መደረግ አለባቸው ብለዋል።
በመድረኩ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳን ጨምሮ፣ በውሃ ሀብት ላይ የሚሳተፉና የሚተገብሩና ከአውሮፓ ሀገራት በፋይናንሰ የሚደግፉ አካላት፣ የሚመለከታቸው ስራ አስፈፃሚዎች፣ አማካሪዎች፣ ከፅ/ቤቶች፣ ከ BRIGHT ፕሮጀክት እና የክልል ውሃ ቢሮ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።