የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተዘጋጁ ሰነዶች በአብይ ኮሚቴ ተገመገሙ።
መጋቢት 17/2018 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ)በሁለተኛው ማእበል ወደ ሪፎርም ከገቡ ተቋማት አንዱ የሆነው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዝግጅት ምእራፍ በየአምዱ የተዘጋጁ ሰነዶችን በከፍተኛ አመራሩ ተገምግሟል።
በዘርፉ በዝግጅት ምእራፍ የተዘጋጁ ሰነዶችን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ጸሀፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የሪፎርሙ ዋና አላማ የተበታተኑ ስራዎችን መሰብሰብ በመሆኑ አሁንም እየተሰሩ ባሉ የዶክመንት ዝግጅት ስራዎች መበታተንና መስፋት እንዳይኖርና ተግባሮችን ስናስቀምጥ ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ እንዳይሆኑ በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል።
በሪፎርሙ ውስጥ የተጠሪ ተቋማት ተግባራት ከሚኒስትሪው የውሃ ሀብት አስተዳደር ተግባር እና ሌሎች ዘርፎች ጋር ተመሳሳይ የስራ ክፍፍል ላይ መጣረስ እንዳይፈጠር ሊተኮርበት ይገባልም ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደ አብይ ኮሚቴ እያንዳንዱ አምድ በሚገባ እየተገመገመ እየተመራ እንደነበር ገልጸው ከበላይ አመራሩ የተሰጡ ግብዓቶችን በመውሰድ ማስተካከያ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
አክለውም እያንዳንዱ የዶክመንት ዝግጅት ስራን በጥልቀት በመገምገም ጊዜ ተወስዶ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ሆኖ በተቻለ መጠን ውጤታማ ስራ ተሠርቷል ብለዋል።
የክቡር ሚኒስትር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ ስራው በጣም አድካሚ መሆኑን ገልጸው የሰው ሀይል አመዳደብ ላይ ሳይንትፊክ በሆነ መልኩ መደራጀቱ ስራው በጥሩ ሁኔታ እንዲከናወን አስችሏል ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ ጊዜ ወስደው ሰራውን በመፈተሽ የሰጡት አስተያየትና ማስተካከያ ለሪፎርሙ ውጤታማነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
እስካሁንም 105 የሪፎርም ሰነዶች የተዘጋጁ ሲሆን የሪፎርሙ የዝግጅት ምእራፍ ሰራ ከ75% በላይ መከናወኑን አክለው ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተጠሪ ተቋማት የአብይ ኮሚቴ አባላት በቀረቡት የሪፎርም ሰነዶች ላይ በተለይም የተቋማቸውን መዋቅር በተመለከተ ከክቡር ሚኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
በቀረቡ ሰነዶችና በአጠቃላይ በሪፎርሙ አተገባበር ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።