ኢትዮጵያ እና ጎረቤቶቿ የጋራ ውሃን ወደ ጋራ ብልፅግና ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ ውይይት ተደረገ።
መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ከአፍሪካ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች፣ ከናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (NBI) ሀገራት የተውጣጡ እና ከፍተኛ የአካዳሚክ ተመራማሪዎች በተገኙበት ኢትዮጵያ እና ጎረቤቶቿ የጋራ ውሃን ወደ የጋራ ብልፅግና እንዴት መለወጥ እንደሚችሉ ተወያይተዋል።
የጋራ የውሃ ሀብትን በተለይም የዓባይን ወንዝ በመቆጣጠር ረገድ ቀጠናዊ ትብብር ያለውን ጠቀሜታ በማጉላት ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው የውሃ አስተዳደር እንዲኖር ሀብትን ለማሰባሰብ በጋራ ርብርብ እንደሚደረግም ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለውን አጋርነት በማጠናከር፤ የውሃ አካላት ደህንነት ማስጠበቅ እና ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘላቂ የውሃ እና የኢነርጂ አስተዳደርን ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት እና የትብብር መድረክ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በየዓመቱ የሚካሄደው የውሃና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የውሃ ልማት ጉዳዮችን የመለየት፣ የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ውይይትን የማጠናከርና የሚዲያውን ተሳትፎ በመጨመር ስለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ፣ በውሃ አስተዳደር ላይ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይም ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም እና በሃይድሮ ፓወር ልማት ላይ ያላትን ተሳትፎ እንደምታጠናክርም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ጥሪውን ተቀብለው ለተሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ ፓናሊስቶችን እና የሚዲያ አካላትን እንዲሁም ለኮንፍረንሱ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።