በሻሸመኔ ከተማ በሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ዘርፍ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጎበኙ።
ሻሸመኔ # መጋቢት16/2018 ዓ/ም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የከተማ ፈሳሽ ቆሻሻ በተቀናጀ መንገድ ማስተዳደር "Integrated waste water and septage management " በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ የተሳተፉ ሰልጣኞች በሻሸመኔ ከተማ በሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ዘርፍ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
የተጎበኙት ፕሮጀክቶች በ4.5 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለውን የሻሸመኔ ከተማ ዘመናዊ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ Faecal sludge treatment plant/ ፕሮጀክት ጨምሮ የህዝብና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ከጋራ መኖሪያ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶች ዙሪያ የተገነባ ሰው ሰራሽ እርጥበታማ ቦታዎች /wetland/ ናቸው።
የስልጠና መርሃግብሩንና የመስክ ጉብኝቱን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከተማ ሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ክትትል ዴስክ ሀለፊ አቶ ገመዳ አበራ የመስክ ጉብኝቱ ያስፈለገው ሰልጣኞች ወደ መጡበት አካበቢ ሲመለሱ ያገኙትን ልምድና ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ በተሻለ ሁኔታ ለመተግበር እንዲያግዛቸው ነው ብለዋል።
አቶ ገመዳ አክለው የክልል ውሃ ብሮዎችም ሆነ የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅቶች ለተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተመሳሳይ በጀትና ጊዜ ተመድቦ የተለያየ አፈፃፀም መኖሩን ገልፀው የሻሸመኔ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ድርጅት በዘርፉ ላመጣው የላቀ ውጤትና ላሳየው ምርጥ ተሞክሮ የሚደነቅና የሚበረታታ በመሆኑ ሰልጣኞች ልምድ መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
በሻሸመኔ ከተማ የ05 የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪና የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ኮሚቴ አባል የሆኑ ወ/ሮ ዙልፋ መሃመድ ከዚህ በፊት ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የሚወጣው ፈሳሽ ቆሻሻ ጉድጓዱን ሞልቶ ወደ ውጭ በመፍሰስ አካባቢውን በማጥለቅለቅ ህብረተሰቡን ለተለያየ በሽታ ይዳርግ እንደነበረ ገልፀዋል።
ወ/ሮ ዙልፋ መንግስት ፈሳሽ ቆሻሻውን በዘመናዊ መልኩ ወደ ሰው ሰራሽ እርጥበታማ መሬት ቀይሮ ካስተካከለ በኋላ ከተለያየ በሽታና ከመጥፎ ሽታ አርፈን ለከብቶች መኖ የሚሆን ሳር በመሸጥ ገቢ እያገኘን ነው በማለት መንግስትን አመስግነዋል።
በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉ ሰልጣኞችም በተመለከቱት ስራ እንደረኩና በቀጣይ ተሞክሮውን ቀምረው በሚሰሩበት ቦታና በሚያስገነቡት ፕሮጀክት በመተግበር የተሻለ ውጤት ለማሳየት እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ስልጠናውን ሙሉ በሙሉ በንቃትና በትጋት ለተሳተፉ ሰልጣኞች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።