የከተማ ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የከተማ ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ሻሸመኔ # መጋቢት 16/2018 ዓ/ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከተማ ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችል"Integrated waste water and septage management" በሚል ርዕስ ለተመረጡ የክልል ውሃ ቢሮና ለከተማ የውሃና ፈሳሽ አገልግሎት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው።   መርሃግብሩ በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የሻሸመኔ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ድርጅት ስራአስኪያጅ ኢ/ር ደምሴ ኞሬ የሻሸመኔ ከተማ በ1903 ዓ/ም እንደተቆረቆረችና የአመሰራረቷን ታሪካዊ ዳራ ካብራሩ በኋላ ስልጠናው በሻሸመኔ ከተማ እንዲካሄድ ዕድሉ ስለተሰጠን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ህዝብ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል። የከተማዋ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለበርካታ ዓመታት ያልዘመነና ኋላቀር እንደነበረ ገልፀው ባለፉት ጥቂት ዓመታት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከከተማው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ጋር በቅንጅት በመስራት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ለሚመለከታቸው አካላት ተሰጥቷል ፣72 የጋራና የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል ስራአስኪያጁ።   ኢ/ር ደምሴ አክለው በከተማው የተገነቡት የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች የከተማውን ጽዳት፣ ውበት ና ምቾት ከማስጠበቅ ባሻገር ሴቶችና ወጣቶች ተደራጅተው በመስራት ኑሮሯቸውን እንዲያሻሽሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷልም ብለዋል። የሻሸመኔ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ድርጅት በሳኒቴሽን መሠረተልማት ዘርፍ የተሻለ አፈፃፀም እንዳለው ገልፀው ስልጠናው ተሳታፊዎች ልምድ የሚለዋወጡበትና ምርጥ ተሞክሮዎችን ቀምሮ ለማስፋት ዕድል የሚገኝበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል። አሰልጣኞቹ ከሀገረ ህንድ ከሳይንስ፣አካባቢና የውሃ ፕሮግራም ማዕከል/Centert of science ,environment & water program /የመጡ ሲሆን በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀት ያካበቱና የማሰልጠን ብቃት እንዳላቸው ተገልጿል ። የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተዘጋጀው ለተመረጡ 8 የክልል የውሃ ቢሮዎች እና 16 የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎቶች ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ሲሆን እንደ ሀገር ከተሞችን ጽዱ፣ማራኪና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችል ነው ተብሏል።   አሰልጣኞቹ ከሳኒቴሽን መሠረተልማት፣ከፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድና መልሶ ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር የሀገራቸውንና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በኢትዮጵያ አውድ እንዴት ተግባራዊ ማድረግና ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ሰፊ ሀሳብ የያዘ ሰነድ ከማብራሪያ ጋር አቅርበው ተሳታፊዎች በውይይት አዳብረዋል ።

Share this Post