ባለፉት አራት ዓመታት በእጅጉ ስኬታማ የሆኑ የሀይድሮ ዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
ቢሾፍቱ : መጋቢት 15/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ሱሉሉታ የውሃና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በዛሬው እለትም ቀጥሎ ውሏል።
ከጋዜጠኞች ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ባለፉት አራት ዓመታት በሀይድሮ ዲፕሎማሲ ስራችን ኢትዮጵያ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን (CFA) ስድስት አገራት እንዲፈርሙ በማድረግ የቆየውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የቀየረ ታሪካዊ ድል ተቀዳጅታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ መልካም ሰራዎችን እየሰራች ፣ውሃ ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠች ባለችበት ሁኔታ አለም አቀፉ ማህበረሰብና ሚዲያው የኢትዮጵያን እውነታ አደብዝዞና የሌሎችን ሀገራት ውሸት አጋኖ የማቅረብ ሁኔታዎችን ለመቀልበስና የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም ለማሳየት ከመረጃ ጋር የተያያዙና የኮሙኒኬሽን ክፍተቶችን በመለየት ከውሃ ጋር በተያያዘ የምናደርጋቸው ንግግሮች አለም በሚረዳው ቋንቋ የማሳወቅ ስራዎች እየተሰሩ ነውም ብለዋል።
በዚህ ዘርፍም የተመረጡ ባህርዳር ፣አርባምንጭ ፣አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች በአባይ እና ህዳሴ ግድብ ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ስራዎችን እየሰሩ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በሀገር ደረጃ በተሰሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች ወደ ተፋሰሱ ሀገራት በመዞር የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ቡሩንዲ፣ደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ጋር በሀይድሮ ዲፕሎማሲው ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በጠንካራ የሀይድሮ ዲፕሎማሲ ስራችን የናይል ወንዝ ኮሚሽን ማቋቋም ችለናል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ይህንን ተቋማዊ ማድረግ ደግሞ ትልቁ አላማችን ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ትኩረቱ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን ወደ ስራ ማስገባት (Operationalize) ማድረግ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የአሰራር ደንቦችን የማዘጋጀትና ዋና መስሪያ ቤቱን የማደራጀት ስራ በኡጋንዳ ሰብሳቢነት እየተከናወነ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ኢትዮጲያ "የውሃ ማማ ናት" የሚለው የተዛባ ትርክት ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እኛው በሰጠናቸው ነገር ላይ ድንጋይ የሚወረውሩበትን አሰራር በመቀልበስ ትርክቱን የመስበር አቋም ተይዞ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የውሃ ሀብትን በመጠንና በጥራት በመጨመር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢኒሸቲቭነት የተተከሉ ችግኞች ና የወንዝ ዳር ልማቶች አበርክቷቸው ከፍተኛ በመሆኑ ባህል ሆነው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።
የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት አዋጅ እና የበር ዞን አዋጅ መጽደቃቸውም ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ነው ክቡር ሚኒስትሩ አክለው የገለጹት።
የቅርብ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ የውሃ ችግር ከሚያጋጥማቸው ሀገሮች አንዷ መሆኗን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግድቦችን በመገደብ መስኖን ማልማትና የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የግድ ነውም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት 81.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ተጠቃሚዎች በየቤታቸው በሮቶ ውሃን ስለሚያጠራቅሙ ፍትሃዊ ስርጭት እንዳይኖር እያደረገ ነውም ብለዋል።
የውሃ ተቋማት በቴክኒክና በኢኮኖሚክስ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ሊመሩ እንደሚገባና የቦርድ አመራሮችም ኃላፊነታቸውን ቀሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ክቡር ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ እንደ ወላይታ ሶዶ፣ አምቦ እና አዳማ ያሉ ከተሞች በጥሩ ተሞክሮ ተጠቃሽ ሆነዋል።
የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሳወቅ ዩኒቨርሲቲዎች በሳይንሳዊ ቋንቋ ጥናቶችን የማሳተም ተግባራት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና የሚዲያ ተቋማትም መረጃዎችን አለም በሚረዳው ቋንቋ በማሰራጨት የተዛቡ ትርክቶችን የማረም ኃላፊነት እንዳለባቸው ክቡር ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።