ለተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር እውን መሆን አረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ነው።
መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ባዘጋጀው ሱሉልታ ውሃ እና ሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በሁለተኛው ቀን የውይይት መድረክ ላይ ለተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር እውን መሆን አረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ነው ተባለ።
"የውሃ ዲፕሎማሲ እና ቀጠናዊ ትብብር ለዘላቂ ውሃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ኮንፈረንስ ቀደም ሲል የተለያዩ ስያሜዎች የነበረው ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ኮንፈረንስ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
በዘንድሮ ዓመት የሚካሄደው ኮንፈረንስ ለየት የሚያደርገው በሀገር ውስጥ ያሉ ምሁራን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራት በመጡ የውሃ ሚኒስትሮች (TAC Members) የተደገፈ በመሆኑ ያላቸውን ልምድና ስለኢትዮጵያ ውሃ ሀብት አስተዳደር የሚያስቡትን በተለያየ አግባብ መገለፁ ነው።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሌላው ዘርፍ ጤናማና ዘላቂ ዕድገት እንዲኖረው ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ለማየት የሚያስችል ኮንፈረንስ ነው ያሉት አቶ ደበበ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዕውን እንዲሆን በአረንጓዴ አሻራ ተፋሰስን (Catchment) የመጠበቅ ስራ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰራችው በአረንጓዴ አሻራ ተግባራት ዳሰሳ ጥናት (Assessment) ተሰርቶ ለዘርፉ ምሁራን የቀረበ ሲሆን ከጎርፍና ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ምን እየተሰራና በቀጣይ በአባይ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ምን መሰራት አለበት፣ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የልማት እንቅስቃሴና የውሃ መገኛ ጥበቃ ላይ ልዩ ስራ መሰራት እንዳለበትም በቀረቡት ፅሁፎች መካተቱንም አቶ ደበበ ጠቁመዋል።
በውይይቱም ወሳኝ የሚባሉና ለትግበራ የሚያግዙ የፖሊሲ ሃሳቦች ይቀርባሉ፤ በተለይ ኢትዮጵያ እየሰራች ካለችው የአረንጓዴ አሻራ ጋር ጎርፍን ወደ ጥቅም በመቀየር ሊሰራባቸው የሚችሉ ትላልቅ ስራዎች በበላይ አመራሩ ቀርቦ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።