ሱሉልታ ውሃ እና ሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ "የውሃ ዲፕሎማሲ እና ቀጠናዊ ትብብር ለዘላቂ ውሃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።

ሱሉልታ ውሃ እና ሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ "የውሃ ዲፕሎማሲ እና ቀጠናዊ ትብብር ለዘላቂ ውሃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው። መጋቢት 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ባዘጋጀው ሱሉልታ ውሃ እና ሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ "የውሃ ዲፕሎማሲ እና ቀጠናዊ ትብብር ለዘላቂ ውሃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር" በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ እየተከበረ ነው።   የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት ኮንፈረንሱ ከአምስት ዓመት በፊት በፎረም ደረጃ የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ላይ ውይይት፣ መግባባትና ትብብርን ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።   በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብና ግልፅ ለማድረግ፤ የምህንድስና እና የውሃ ዲፕሎማሲን ብሎም ስለዓለም አቀፍ የውሃ ህግና ዲፕሎማሲ ላይ ግንዛቤን ለማዳበር ያለመ ኮንፈረንስ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብታችን ላይ በድርድር እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ብሔራዊ አቅምን በመገንባት ስለውሃ ሀብት ግንዛቤ እንዲኖር የሚያግዝና ከአጎራባች ሀገራት በውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያም የመማማሪያ መድረክ ነው ብለዋል፡፡   ኮንፈረንሱ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ቀድሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰው፤ በየዩኒቨርሲቲው በዙር መዘጋጀቱንም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ በልዩ ተኮላ በበኩላቸው ኮንፈረንሱ የውሃ አስተዳደርንና ቀጠናዊ ትብብርን በጋራ በማጎልበት ከወሰን ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ተጋሪ ሀገራት ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያግዛል፤ በዘርፉም ያሉ ልምዶችንም ለማስፋት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።   በመድረኩ 34ኛው የአለም የውሃ ቀን "ውሃና ስርዓተ ፆታ" በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን የNBI ቴክኒካል ኮሚቴን ጨምሮ ከIWRM እና WLRC, የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ አለማየሁ አሰፋ፣ የአፍሪካ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች ታድመው፤ የውሃ አቅርቦትና እጥረት እንዲሁም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር በኢትዮጵያ በሚል ርዕሰ ጉዳይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

Share this Post