አባይ የትብብር እንጂ የልዩነት ምንጭ አይደለም ሲሉ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
ቢሾፍቱ: መጋቢት 14/2018ዓ.ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፉ የውሃና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስን በይፋዊ ንግግር ከፍተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ እና በአባይ ተፋሰስ አገራት የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ (TAC) ላይ ባደረጉት ይፋዊ የመክፈቻ ንግግር የናይል ተፋሰስ የጋራ ግንኙነት በፖለቲካዊ ሳይሆን በሳይንሳዊ እና በቴክኒካዊ መንገድ ሊመራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ውሃን ከፖለቲካ ነፃ በማድረግ በሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ትብብር መፍጠር ለሁሉም ሀገራት ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
"እምነት የሚገነባው በስብከት ሳይሆን በተግባርና በማስረጃ ነው" ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የተፋሰሱ ሀገራት እንደ ድርቅና ጎርፍ ባሉ የጋራ ተግዳሮቶች ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጅቡቲ የምታደርገው የውኃ አቅርቦት ትልቅ የትብብር ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ፣ የህዳሴ ግድብም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሱዳን እና ግብፅ የጎርፍ መከላከልና የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ አስረድተዋል።
ግድቡ የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ትስስርን በማጠናከር ለጋራ እድገት የሚውል እንጂ የማንም ስጋት አለመሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ውሃውና አካባቢው ካልተጠበቀ በታችኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ የውሃ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም የተፋሰስ ጥበቃ የጋራ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደሩ ያሉት ጫና ከፍተኛ በመሆኑ አሁኑኑ ጠንካራ የትብብር መሰረት መጣል የግድ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑና የሚዲያ ባለሙያዎችም ከሳይንቲስቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ባጠቃላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አባይ ለቀጠናው ሀገራት የቤተሰባዊ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ምንጭ እንዲሆን ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አስታውቀዋል።
በመርሃ ግብሩ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የታንዛኒያ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮችና የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ ሴክሬተሪያት መልእክት አስተላልፈዋል።
መርሃ ግብሩ በነገው እለትም ቀጥሎ ይውላል።