የዓለም የውሃ ቀን እና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

የዓለም የውሃ ቀን እና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው። ​ ቢሾፍቱ መጋቢት 14/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2026 ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን "ውሃ በሚፈስበት ቦታ እኩልነት ያድጋል" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው። ​ በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ​ያደረጉት ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ንጹህ ውሃ የማግኘት ጉዳይ ከሰብአዊ መብት ባለፈ ከጾታ እኩልነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው ገልጸዋል። ክቡር ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 1.8 ቢሊዮን ገደማ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማይያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል ። ​ሴቶች ውሃ ለመቅዳት ከወንዶች በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ጊዜ እንደሚያጠፉ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም በሴቶች የትምህርት፣ የጤና እና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑንአስገንዝበዋል። ​ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት ባከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሏን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ81.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ንጹህ ውሃ የሚያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 51% ፣በውሃና ሳኒቴሽን (WASH) ኮሚቴዎች ውስጥ 56% ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ​ በፕሮግራሙ ላይ ​​"የውሃ አስተዳደር ለሥርዓተ-ጾታ እኩልነት እና ለሴቶች አቅም ግንባታ" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ከናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (NBI) እና ከአለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት (IWMI) የተወከሉ ምሁራን ሙያዊ ትንታኔ አቅርበዋል። ንጹህ ውሃን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የሴቶችን ጫና ከመቀነስ ባለፈ፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል። በኮንፈረንሱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ፣የደቡብ ሱዳን፣ የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ እና የቡሩንዲ የውሃ ሚኒስትሮችና ተወካዮች የውሃ፣ መስኖና፣ ቆላማ አካቢዎችናየአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፣የዘርፋ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

Share this Post