የደንበል ሀይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ የሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነት መሆኑ ተገለጸ።

የደንበል ሀይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ የሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነት መሆኑ ተገለጸ።   "መጤ የእንቦጭ አረምን ከደንበል ሃይቅ ላይበጋራ እናስወግድ!! "በሚል መሪ ቃል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ልማት ጽ/ቤት ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በጋራ በተዘጋጀው የህብረተሰብ ንቅናቄ ላይ የደንበል ሀይቅን መጠበቅ የሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነት መሆኑ ተገለጸ።   ባቱ:-ጥር14/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የባቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ኡስማን ተሴ በከተማዋ የሚገኘው የሀሬ ደንበል ሀይቅ ዳርቻ ላይ ያለውን የእንቦጭ አረም ለመታደግ ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   ምክትል ከንቲባው አረሙ ከሀይቁ 64 ሄክታር በላይ የሸፈነበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ የሚመለከታቸውን አካላትን በማስተባበር የደንበል ሀይቅን ለመታደግ እየሰራ ነውም ብለዋል። ከዚህም በፊት የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ኢንቨስተሮችን፣ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት እና ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ54ሄ ክታር በላይ አረም በማስወገድ ትልቅ ስራ መሠራቱንም አውስተው አሁን ላይ የተጀመረውን ስራ ህብረተሰቡ በመረዳት በሳምንት ሁለት ቀን እየወጣ አረሙን ለማጥፋት እንደሚሰራ አክለው ገልጸዋል።   በመጨረሻም ምክትል ከንቲባው ለዚህ ስራ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ አካላት ዳርቻን ከመጠበቅ አኳያ መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል ። የአካባቢ ጥበቃ ባቱ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ብዝየ ቶላ የመርሀግብሩ አላማ የደንበል ሀይቅን ከመጤ አረም ለመጠበቅ ታሳቢ ያደገረ መሆኑን ገልጸው አረሙ በሀይቁ ላይ ከታየበት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።   ወ/ሮ ቡዝየ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ልማት ጽ/ቤት ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያስጀመረው ዘመቻ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ የሚመለከታቸው አላካት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ሀይቁን ከጥፋት ለመጠበቅ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ልማት ጽ/ቤት ዝዋይ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ሰለሞን በልሁ ንቅናቄው ማህበረሰቡን በማሳተፍ የአንቦጭ አረምን ከደንበል ሀይቅ ለማስወገድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።   ከዚህ በፊት ባደረጉት ንቅናቄ አረሙን በማስወገድ ውጤታማ ስራ በመሰራቱን በእንቦጭ አረም ምክኒያት የጠፋው ፊላ ሳር ተመልሶ የበቀለበት ሁኔታ መኖሩንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። በአካባቢው ያሉ የአበባ አምራቾች ቦታ በመውሰድ የእንቦጭ አረም የማስወገድ ስራ በተቋማት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሰለምን ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ሀይቁን የመጠበቅ ሀላፊነት ስላለበት በተለይ የውሃ አካላት ዳርቻን በማስጠበቅ እና ሀላፊነቱን በመወጣት ሀይቁን መታደግ አለበት ብለዋል።   የንቅናቄው ተሳታፊዎችም ሀይቁን ከመጥፋት ለመታደግ በተለይ አረሙን ሊያስፋፉ የሚችሉት ነገሮች በቅድሚያ ማስወገድና የሀይቁን ዳርቻ መንግስት ሊያስከብር ይገባል ብለዋል።

Share this Post