ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገ የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ።

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገ የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ ። ጥር 05/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገ ኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር በቢሯቸው ውይይት አደረጉ።   በውይይቱ ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፎች የተከናወኑ በርካታ ስራዎችን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለአባላቱ በስፋት አስረድተዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ አገልሎት ላይ የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ ከለውጡ በኃላ በርካታ ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ጥሩ ዕድል እንደፈጠረም አስገንዝበዋል።   ኢትዮጵያ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ገበያም ኃይልን ለመላክ አቅዳለች ያሉት ክቡር ሚንስትር ዴኤታው የግሉን ዘርፍ በሀገሪቱ የሀይል ልማት መስክ ማሳተፍ ለጥራት፣ ለኃይል ማመንጫ እና ለኤክስፖርት እንዲሁም በተወዳዳሪ ዋጋ ኃይልን ለማቅረብ ያለውን አበርክቶ በአፅንዖት አስረድተዋል። አያይዘውም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ንፁህ ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ የምትልክ እና ለቀጠናው መረጋጋት እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ አስተዋጽኦ የምታደርግ ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ መሆኗንም አጉልተው ገልጸዋል።   ኢትዮጵያ ከሌሎች የቀጠናው ሀገሮች ጋር እኩል ማደግ እንደምትፈልግ የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለሌሎችም አስፈላጊ የሆነውን ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት ለማስፈን ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ እና ይህንንም ጥረት ከፍ ለማድረግ በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረገች ነው ብለዋል። የቻምበሩ አባላትም ክቡር ሚኒስትር ዴታው የተናገሩትን ሃሳብ እንደሚደግፉና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተመረቀበት ጊዜ ጀምሮ ምክር ቤቱ የሚያገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በቅርበት ሲያጤኑ እንደቆዪ ገልጸው ኢትዮጵያ በቅርቡ ከመሪ የኃይል ዲፕሎማቶች አንዷ ትሆናለች ብለዋል።   ከራሳቸው የንግድ ፍላጎቶች በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገሪቱ እና ለሌሎችም ሀገራት ባመጣው ትልቅ የኢንቨስትመንት እድል በመነሳሳት ከግድቡ የኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ስላለው ሰፊ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አቅም ለዲያስፖራው ማህበረሰብ እና በአሜሪካ ውስጥ ላሉ ባለሀብቶች ለማሳወቅ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም በሚያዝያ 2018 ዓ/ም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ትኩረት ያደረገ ትልቅ ሲምፖዚየም በአሜሪካ የማዘጋጀት እቅድ እንዳላቸውም ይፋ አድርገዋል።

Share this Post